የሕይወት ተስፋ!
- Redeatu G. Kassa
- Oct 18, 2015
- 2 min read
የሕይወት ተስፋ! “በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚሆን የሕይወት ተስፋ፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።” (2 ጢሞ. 1፡1-2) ከላይ በሰፈረው ሰላምታ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ አንድ መሰረታዊ የክርስትናን አስተምህሮ ሲጠቅስ እንመለከታለን። የኸውም “በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚሆን የሕይወት ተስፋ” በሚለው ሃረግ ውስጥ እንደተቀመጠው የሕይወት ተስፋ ያለው በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ የሚገልጸው ክፍል ነው። ሐዋሪያው በመንፈስ ልጁ ለሆነው ለጢሞቲዎስ በጻፈው በዚህ ሁለተኛ ደብዳቤ ለየት ባለ መልኩ ሰላምታውን ስለ ህይወት ተስፋ በመግለጽ ይጀምራል። የምድር ሕይወቱና አገልግሎቱ በክርቶስ ኢየሱስ ባለ የሕይወት ተስፋ ላይ የቆመ እንደሆነ ያጸናል። ያለበትንም ሁኔታ የሚመለከተው ከዚህ የሕይወት ተስፋ አንጻር ነው። ለመሆኑ ህይንን ደብደቤ ሲጽፍ ሐዋሪያው በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ነበር። ይህንን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ሐዋሪያው በኔሮ አስተዳደር በሮም ታስሮ የነበረበት ወቅት ነው። ስለዚህም በቁጥር 8 ላይ ልጁን ጢሞቲዎስን “በእስረኛው በእኔ አትፈር” ይለዋል። እንደዚሁም ወንጌልን በመስበኩ እንደ ክፉ አድፋጊ እንደታሰረ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንደማይታሰር ይናገራል። (1ጢሞ. 2፡9) ብዙዎችም ከርሱ ፈቀቅ እንዳሉና በብቸኝነት ያለበት ጊዜም እንደሆነ ክፍሉ ይጠቅሳል። (“በእስያ ያሉቱ ሁሉ ከእኔ ፈቀቅ እንዳሉ ታውቃለህ” (2ጢሞ. 1፡15))። ዴማስ ይኅንን አለም ወዶ ትቶታል፤ ሌሎችም ትተውት ወደ ተለያየ ስፍራ ሄደዋል፤ አንጥረኛው እስክንድሮስ እጅግ ከፍቶበታል፤ እንዲሁም በፊተኛው ሙግቱ ማንም አልደረሰለትም -- ሁሉም ትተውታል። (2ጢሞ. 4፡ 9-17) በዚህ ሁሉ ግን ሐዋሪያው በምሬትና በትስፋ መቁረጥ ውስጥ ሳይሆን ያለው ይልቁንም የኖረለትን፣ የቀመሰውንና የሚመጣውን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን የሕይወት ተስፋ እያሰበ ከመከራው በላይ ሆኖ መክበሩን ይጠባበቃል። በተለይም ደግም ሐዋሪያው ይህንን ክፍል ሲጽፍ በምድር ያለው አገልግሎቱ እየተጠናቀቀ እንደሆነ አውቋል። (“በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል።” (2ጢሞ. 4፡6) ነገር ግን የሚጽፈው ስለሞት ሳይሆን ስለ ሕይወት ነው። የሚጽፈው ስለ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ስለ ተስፋ ነው። እንዲያውም የተጠበቀለትን አክሊል እያሰበ ደስ ይለዋል። በብዙም ያመሰግናል። ማንም አጠገቡ ባይኖርም ጌታ ግን ከርሱ ጋር እንዳለና የጌታ ሃሳብ በርሱ እንደሚፈጸም ያውቃል። (“ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ፥ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ። ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” 2ጢሞ. 4፡ 17-18)) የጳውሎስ ትኩረት በመክራው ላይ ሳይሆን በተገለጠውና ሊገለጥ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው የሕይወት ተስፋ ላይ ነበር። መከራውንም ያስረሳው ሕይወቱ በዚህ የሕይወት ተስፋ ብረሃን በመሞለቱ ነበር። መጽሐፍ እንደሚለን ጌታችን የመጣው ሕይወት እንዲሆንልንና እንዲበዛልን ነው። (ዮሐ. 10፡10) ጨለማውን ሊያሸንፍ የሚችል ሕይወት ያለው በእርሱ ብቻ ነው። (ዮሐ. 1፡5) በኛ ውስጥ የክርስቶስ ሕይወት ስላለ ጨለማ ሊውጠን አይችልም። የሐዋሪያው ትምክህት በክርስቶስ ባለ የሕይወት ተስፋ ነበር። የኛስ?
Recent Posts
See All“ተስፋን ቃል የሰጠዉ የታመነ ነዉና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ። (ዕብ 10፡ 23) ተስፋ ሰው በሕይወቱ እንደሚሆን በእርግጠኝነት የሚጠብቀው ነገር ነው። እያንዳንዱ ሰዉ ተስፋ የሚያደርገዉ...
ባለንበት ጊዜ በተለይም በ COVID 19 ወረርሽኝ የተነሳ በአብዛኛው ቤት ውስጥ ተከተን ባለንበት በዚህ ወቅት፤ የተለያየ ድምጽ፣ አስተሳሰብ፣ ጩኸት፣ አመለካከት እና ፕሮፓጋንዳ የምንሰማበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በተለይም...
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በምእራቡ አለምና በሃገራችን በኢትዮጲያ በተወሰነ መልኩ በትምህርት ቤቶች፣ በአንዳንድ ቢሮዎች፣ በቤትና በአፓርትመንት መስኮቶች ላይ በወረቀት የተቀለመ ህብረቀለማትን አዋህዶ የያዘ...
Comentarios