top of page

የተለየ መንፈስ!

“አገልጋዬ ካሌብ ግን የተለየ መንፈስ ስላለውና በፍጹም ልቡ የተከተለኝ በመሆኑ ሄዶባት ወደ ነበረችው ምድር አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ይወርሷታል።” (አመት ዘኁ. 14፡24)

በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሰረት ሙሴ እስራኤል ይገባበት የነበረውን ምድር እንዲሰልሉ አስራ-ሁለት የነገድ አለቆችን ወደ ከንዓን ምድር ላከ። (ዘኁ. 13) ከተላኩት አስሩ ለማህበሩ ያመጡት ያአሰሳ ውጤት ድብልቅ ነበር። በአንድ በኩል ምድሪቱ “ማርና ወተት” የምታፈስስ ናት ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ የምድሪቱ ሰዎች “ኃያላን” ናቸው፤ ከተሞቹም የተመሸጉና ትላልቅ ናቸው በማለት የሕዝቡን ልብ አቀለጡ። ካሌብ ግን ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ “እንውጣ! ምድራቸውንም እንውረስ ማሸነፍም እንችላለን” አላቸው። አስሩ ግን “ልናቸንፋቸው አንችልም ... ያየናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ናት ... በነርሱ አይን እንደ አንበጣ ነን” አሉ። የሕዝቡ ልብ እጅግ በወደቀና በአመጽ መንፈስ ወደ ግብጽ እንመለስ ባሉ ጊዜ ኢያሱና ካሌብ በማህበሩ ፊት ልብሳቸውን ቀደው “ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት። እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው” ሕዝቡን ተናገሩ። በተመለክትነው ክፍል ልዩነትን ያመጣው ኢያሱና ካሌብ የተለየ መንፈስ ስለነበራቸው ነው። ይህ የተለየ መንፈስ የእምነት መንፈስ ነው። ኢያሱና ካሌብ ምድሪቱን በራሳችን ብርታት እንወርሳለን አይደለም ያሉት። የነርሱ ብርታት በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው እምነት ነው የመነጨው። እግዚአብሔር ደስ ከተሰኘብን ያወርሰናል አሉ። እግዚአብሔር ከኛ ጋር ነው አሉ። ወገኖቼ፦ ሁልጊዜም ብርታት የሚሰጠን እግዚአብሔር ከኛ ጋር እንደሆነ ስንረዳና ስናምን ነው። ለዚህ ነው ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል የሚለን። በኢያሱና በካሌብ የነበረው የተለየ መንፈስ የአመለካከት ልዩነትን የሚሰጥ መንፈስ ነው። የሚገርመው አስሩ ሰላዮችና ኢያሱና ካሌብ የተመለከቱት አንድ ምድር፤ ያዩትም አንድ አይነት ሰዎች ነበሩ። ልዩነቱ አስሩ ትኩረታቸው የችግሩ ግዙፍነት ላይ ሲሆን ኢያሱና ካለብ ግን ትኩራታቸው በአምላካቸው ትልቅነት ላይ ነበር። ልዩነቱ የአመለካከት ልዩነት ነበር። ምንጊዜም ቢሆን አይናችንን ከጌታ ላይ አንስተን በከበበን ነገር ዙሪያ ላይ ስናደርግ መስጠም እንጀምራለን። ችግሩ እምነታችንን ይጋርደዋል። ነገር ግን በእምነት አይኖቻችን ከኛ ጋር ያለውን ስናይ ችግሩ ትንሽ አምላካችን ትልቅ መሆኑን ተረድተን በጌታችን እንጓደዳለን። ወገኖቼ፦ የተሰጠን መንፈስ የልዩነት መንፈስ ነው። ፍርሃት ባለበት ድፍረትን ይሰጠናል፤ በጭንቀት መኃል ያረጋጋናል፤ በሃዘን መሃል በልባችን ደስታን ያፈስልናል፤ በድካም ያበረታናል። የልዩነት መንፈስ! አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page