top of page

ሰራተኛው መንፈስ!

መንፈስ ቅዱስ አሁን በስራ ላይ ነው። መንፈስ ቅዱስ በፍጥረት መጀመሪያ በስራ ላይ እንደነበረና ለምድር ቅርጽ፣ ሙላትና ሕይወት ይሰጥ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም አማኞችን (የክርስቶስን ሙሽራ) እየሰራ ነው ያለው። ክርስትና የመገለጥ ጉዳይ ነው። ይህንን መገለጥ ደግም የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ነው። ስለዚም ነው ሐዋሪያው ጳውሎስ ለኤፊሶን ቅዱሳን አብን ይበልጥ ያውቁት ዘንድ የጥበብና የመገለጥ መንፈስ እንዲሰጣቸው የሚጸልየው። (ኤፌ 1፡17) ስለ መንፈሳዊ እውነት መገለጥን የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ነው። (“መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው።” (1ቆሮ 2፡10) መንፈስ ቅዱስ እውነትን ያስተምራል፣ ያሳስባል፣ ይገልጣል። እርሱ የእውንት መንፈስ ነው። (ዮሐ. 14፡25፣ 16፣12) ቃሉን የሚያስተምረን መንፈስ ቅዱስ ነው። ለዚህም ነው በትንቢተ ኢሳያስ ላይ “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” (ኢሳ 54፡13) በማለት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን። በአዲስ ኪዳንም ሐዋሪያው ጳውሎስ ይህንኑ ያረጋግጥልናል። (“እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ” (1ዮሐ 2፡20)፤ “እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።” 1 ዮሐ 2፡27) መንፈስ ቅዱስ በኛ ውስጥ ሆኖ ስለ ክርስቶስ ይመሰክራል። (የሐ. 15፡ 26) ብቻችንን የክርስቶስ ምስክሮች መሆን አንችልም። ስለ ክርስቶስ የንመሰክረው መንፈስ ቅዱስና እኛ ነን። ለዚህ ነው በሐዋ 1፡8 ላይ ቃሉ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” የሚለን። መንፈስ ቅዱስ በኛ ላይ ሲወርድ ምስክር አለመሆን አይቻልም። መንፈሱ ለክርስቶስ ምስክር ለመሆን የሚያስፈልገንን ኃይል፣ ጥበብና ማስተዋል ይሰጠናል። ቃሉ እንደሚያረጋግጥልን መንፈስ ቅዱስ ወደረኞቻችን ሁሉ ሊቃወሙትና ሊከራከሩት የማይችሉት ጥበብና አፍ ይሰጠናል። (ሉቃስ 21፡15) ሰማእቱ እስጢፋኖስ የሚናገርብትን ጥበብ ሊቋቋሙት ያልቻሉት በርሱ ውስጥ ሆኖ ከሚመሰክረው መንፈስ የተነሳ ነበር። (ሐዋ 6፡10) መንፈስ ቅዱስ በኛ ውስጥ ሆኖ አለምን ስለ ኅጢያት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ይወቅሳል። (ዮሐ. 16፡7) ኖህ አለምን በጽድቅ ኑሮው እንደኮነነ ሁሉ በክፉና በጠማማ ትውልድ መካከል ስንኖር መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን ኃይልና ብቃት የአለምን ኀጢያት እንገልጻለን። በኛ ያለው ብረሃን ጨለማን ይገልጣል -- መጽሐፍ “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ” እንደሚል። መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን የክርስቶስን መአዛ ይገልጣል። (2ኛ ቆሮ 2፡ 14-16) መንፈስ ቅዱስ በኛ ያለውን አዲሱን ሰው እንዲገልጥ ከርሱ ጋር የበለጠ ሕብረት ማድረግ ያሻናል። እግዚአብሔር ይረዳናል። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page