እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔን እናመልካለን።
“እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” (ኢያሱ 24፡15) ኢያሱ የምድር አገልግሎቱን ፈጽም ወደ አምላኩ ከመሰብሰቡ በፊት የእስራኤልን አለቆች ሰብሰቦ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን አሳሰባቸው። (ኢያሱ 24) እግዚአብሔር አብረሃምን ጣኦትን ከሚያመልክበት ከኡር ምድር አውጥቶ ባረከው። እግዚአብሔር በጸናች ክንድ ሕዝቡን ከግምጽ ምድር ከባርነት አወጣው። ዮርዳኖስንም አሻግሮ ባለ ርስት አደረገው። ሕዝቡ ያልደከሙበትን ምድር ወረሱ፤ ባልሰሩትም ከተሞች ኖሩ፤ ያልተከሉትንም ወይንና ወይራ በሉ። እግዚአብሔር ሕዝቡን በንስር ክንፍ ተሸከመ። እናም ኢያሱ እስራኤልን ሲመክር “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት” (ቁ. 14) አላቸው። የአሕዛብ አማልክቶችንም ከእነርሱ እንዲያርቁ አዘዛቸው። ነገር ግን እግዚአብሔርን ማምለክ ክፉ መስሎ ከታያቸው የሚያመልኩትን እንዲመርጡ — ከባርነት ቀንበር ፍትቶ የራሱ ህዝብ ያደረጋችሁን እግዚአብሔርን ወይስ አጋንቶች የሆኑትን የአህዛብ አማልክትን ታመልካላችሁ። የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ በማለት በሁለት ሃሳብ ከሚያነክስ ሕይወት እንዲወጡ ፊት ለፊት ገሰጻቸው። ወገኖቼ የዳነው እግዚአብሔርን ለማምለክና ለማገልገል ነው። እግዚአብሔር በጸናችና በተዘረጋች ክንድ እስራኤልን ያመልከውና ያገለግለው ዘንድ ከግብጽ ምድር እንዳወጣው ሁሉ እኛንም በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የእዳ ጽሕፈታችንን ደምስሶ በሕይወት ያኖረን እናመልከውና እናገለግለው ዘንድ ነው። ወደ ጌታ ስንመጣ የነብሳችን ሸክም ተወግዶልናል። ከባዱን የኃጢያትና የሞት ቀንበር ከላያችን ከተነሳልን በምትኩ ቀላሉን የጌታን ቀንበር መሸከም አለብን። የዳንነው ለእረፍት ብቻ ሳይሆን ለአምልኮና ለአገልግሎትም ጭምር ነው። አምልኮ የምርጫ ጉዳይ ነው። ሰው ሁሉ አምላክ (ጣኦት) አለው። አንዳንዱ ሰው ስራውን ያመልካል፤ ሌላው ደግሞ ገንዘብን የሚያመልክ አለ። በአንጻሩ ደግሞ ስልጣን ወይንም ዝና አምላኩ የሚሆንለት አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር የማይመለክበት ክብር፣ ገንዘብ፣ ስልጣን ... ወዘተ ምንጩ ሌላ አምላክ ነው። ዲያብሎስ ስግደትን ይፈልጋል። ይመለክና ይሰገድለት ዘንድ ደግም የምድርን ሃብት፣ ክብርና ዝና ሁሉ ሊሰጥ ይችላል። ወይንም በአለም ባለው ሃብት፣ ክብርና ዝና ወድቀው ይሰግዱለት ዘንድ ሊደልል ይችላል። ነገር ግን እንደ ጌታ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ “ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል” ብለን ማበረር መቻል አለብን። እግዚአብሔር በግድ ሳይሆን በምርጫ የሚመለክ ነው። እግዚአብሔር ነጻ ፍቃደን ሰጥቶናል። በፍቃዳችንን ራሳችችንን ለእርሱ እንድንቀድስና እርሱን ብቻ እንድናመለክ ይፈልጋል። የምናመልከውን ዛሬ እንምረጥ።