top of page

“ቦነስ” ይጨመራል።

“ነእንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ...ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴ. 6፡33) አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ለሰራቶኞቻቸው በአመቱ መጨረሻ ቦነስ ይሰጣሉ። ቦነስ ደመወዝ አይደለም። ነገር ግን በደመወዝ ላይ የሚጨመር ነው። ሰራተኛም ሲሰራ የሚሰራው ለቦነስ ሳይሆን ለደመወዝ ነው። ነገር ግን መስሪያ ቤቱ ትርፋማ ከሆነ የሰራተኞቹን በጎ ጥረት ለማመስገን ቦነስ ሊሰጣቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ነገር እንድፈልግ ይመክረናል። ለክርስቲያን ዋና ነገር የእግዚአብሔርን ጽድቅና መንግስት መፈለግ ነው። ይህ ማለት እግዚአብሔር ቅድሚያ ያደረግ ሕይወት ማለት ነው። በሕይወታችን ዋና ያደረግነው ነገር እግዚአብሔርን መፈለግ ከሆነ እግዚአብሔር ከሚያስፈልገን ነገር ሁሉ አያጎድለንም። እኛ እግዚአብሔርን ስንፈልግ እግዚአብሔር ደግም አባት ነውና ለልጆቹ በምድር የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያዘጋጃል። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ማን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? እያልን እንዳንጨነቅ ያስተምረናል። ለእነዚህ ጉዳዮች የሚጨነቁት የማያምኑ ሰዎች ናቸው። የዚህ አለም ሰዎች ትልቁ የሚኖሩበት አላም ምድራዊ ፍላጎትን ለማሳካት ነው። ሕይወታቸውን የሚመራው የማይሞላ የፍላጎት ቋት ነው። ፍላጎት አይረካም። ሁልጊዜ እልፍ ብሎ የሚገኝ ኢላማ ነው። ስለዚህ የማያምን ሰው የሕይወቱ አላማ ምድራዊ ከሆነው ነገር አያልፍም። ክርስትና ግን የሚጀምረው ከሙላት ነው። በብሉይ ኪዳን ንጉስ ዳዊት “እግዚአብሄር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 23፡1) መዝሙረኛው የሚለው እግዚአብሔር ካለኝ ሙሉ ነኝ። ፍላጎቴ ረክቷል ነው። ሰው ፍላጎቱ የሚረካው በእግዚአብሔር ላይ ሲያርፍ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ያለው ሰው መሰማሪያ አለው፣ የእረፍት ውሃ አለው፣ ጥበቃ አለው፣ ሰላም አለው፣ በረከት አለው፣ ተስፋ አለው ... ሁሉ አለው። በአዲስ ኪዳንም መጽሐፍ ቅዱሳችን በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ እንደተባረክን ይናገራል። (ኤፌ1፡3) ቃሉ የሚለው እንባረካለን ሳይሆን ተባርከናል ነው። አሁን ተባርከናል። አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን። አሁን በክርስቶስ ደም ቤዛነት አግኝተን ጸድቀናል። አሁን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናል። አሁን አይምሮን ሁሉ የሚያልፍ ሰላም አለን። አሁን በመንፈስ ቅዱስ ታትመናል። አሁን ለትልቅ ተስፋ ተጠብቀናል። አሁን ተባርከናል። ወገኖቼ፦ እኛ የምንኖረው ሕይወት እግዚአብሔርን ራሱን ማለትም የርሱን ጽድቅና መንግስት የሚፈልግ ነው። ይህ ሲሆን ቦነሱ (የሚበላው፣ የሚጠጣው፣ የሚለበሰው፣ ትዳሩ፣ ስራው... ወዘተ) ይጨመራል። እንደ አብርሃም እግዚአብሔርን ከመረጥን። ቀኙም፣ ግራሙም ለምለም ነው። ለእርሱ እንጂ ለበነሱ አንኑር። እግዚአብሔር በማስተዋል ይባርከን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page