top of page

12ቱ ደቀመዛሙርት -"ክርሰቲያን ወይስ ደቀመዝሙር?"

ኢየሱስ የሰውን ሥጋ ለብሶ እኔና እናንተ ወዳለንበት ወደዚች ምድር የመጣው የምሥራቹን ቃል በማብሠር በጨለማ የተቀመጥነውን እኛን ወደሚደነቅ ብርሃን ለማውጣት፣ ዲያቢሎስ የጫነብንን የኃጢአትና የሞት ቀንበር በመስቀል ላይ ስለ እኛ በመሞት ካስወገደው በኋላ እኛን ከአብ ጋር በማስታረቅ የዘላለምን ህይወት በርሱ በማመን ብቻ እንድናገኝ ለማድረግ ነው። ወንጌል ማለት በአጭር ቃል - ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን እንደሞተ፣ እንደተቀበረና በሦስተኛው ቀንም እንደተነሳ ማመን ማለት ነው። በሌላ አባባል ወንጌል የምሥራች ማለት ነው - ይህም - ኃጢአተኛው ካሁን በኋላ በኃጢአቱ እንዳይሞት ኢየሱስ በኃጢአተኛው ምትክ ስለሞተ ነጻ ወጥቷል ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ይህንን የምሥራቹን ወንጌል ለዓለም ሁሉ ለማድረስ ከተጠቀመባቸው መንገዱች አንዱ ደቀመዛሙርትን ማዘጋጀት ነበረ። በአይሁድ ባህል መሠረት ዕድሜው 30 ሲሆን የውጭ አገልግሎቱን በይፋ ለመጀመር አስቀድሞ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ ተጠመቀ። በመቀጠልም በመንፈስ ተመርቶ ወደ ምድረበዳ በመሄድ ዲያቢሎስ ያቀረበለትን ፈተና "ተብሎ ተጽፏል!" በማለት በቃሉ ካሸነፈው በኋላ ካደረጋቸው የመጀመሪያ ነገሮች አንዱ 12ቱን ደቀመዛሙርት መምረጥ ነበር (ማቴ 4፤ ማር 1) ደቀመዝሙር ማለት የቃሉ ትርጉም ተከታይ ወይም ተማሪ ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ የጌታውን ዱካ በቅርበት እየተከተለ የእግሩን አቧራ እየጠጣ የሚከተል ማለት ነው። ምንም እንኳን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች ኢየሱስን ቢያጅቡትም ወይም ቢከተሉትም፤ እርሱ ግን 12ቱን ደቀመዛሙርት የመረጠበትን ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ሲገልጽ፦ "ከርሱ ጋር እንዲኖሩና ወንጌልን ለመስበክ እንዲልካቸው" ነበረ ይላል (ማር 3:14)። ዛሬም በዘመናችን ብዙ ሰዎች ስለ ሃይማኖታቸው ሲጠየቁ ክርስቲያን እንደሆኑ ይናገራሉ፤ ነገር ግን ህይወታቸውና ኑሯቸው እንደቃላቸው እውነተኛ ክርስቲያን ወይም የክርስቶስ ተከታይ መሆናቸውን አያመለክትም። በጌታ ኢየሱስ ያመንን የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ የተጠራነው ለሁለት ዋና ነገሮች እንደሆነ ከማር 3:14 መማር እንችላለን። የመጀመሪያው:- ከርሱ ጋር ለመኖር ነው የተጠራነው። ከኢየሱስ ጋር በመኖር ቃሉን ሲሰሙና ሥራውን ሲመለከቱ ደቀመዛሙርቱ ህይወታቸው እንደተለወጠ፤ የኛም ህይወት እንደ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ የሚለወጠውና ወደክርስቶስ መምሰል የሚያድገው በየዕለቱ ከርሱ ጋር ቃሉን በማንበብና በመጸለይ ስንኖር ነው። ሁለተኛው:- ወንጌልን ለመስበክ ነው የተጠራነው። ደቀመዛሙርቱ የተጠሩበት ዓላማ የምሥራቹን ቃል ለፍጥረታት ሁሉ ለማድረስ እንደሆነ ስለተረዱ ምንም ሳያንገራግሩ ሁሉን ትተው ኢየሱስን በመከተል እርሱ የጀመረውን ሥራ ቀጥለው ለመሥራት እንደቻሉ በወንጌላት እናነባለን። ወገኖቼ፤ በየትኛውም ዓይነት ሥራ ውስጥ ብንሠማራም እኛም የተጠራነው ለራሳችን ተደላድለን ምድራዊን ኑሮ ለመኖር ሳይሆን ለሌሎች የወንጌልን ቃል በመናገርና ብርሃናችንን በማብራት በጨለማው ገዥ ሥር ያሉትን ሰዎች ወደ ጌታችን መንግሥት በማምጣት የከበረ ሥራ እንድንሠራ ነው።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page