እርሱ ስለኛ ሞተ!
“ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።” (ሮሜ 5፡8)
ሊ ስትሮብል የተሰኘው ከኢአማኒነት ጌታን ወደ ማወቅና ማምለክ የመጣ ጋዜጠኛና ደራሲ ስለ ተስፋ በጻፈው መጽሐፉ ላይ ሌላ ደራሲን በመጥቀስ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጊዜ በጃፓን ተማርከው ስለነበሩ የአላይድ (Allied) ጦር ወታደሮች ይናገራል። ምርኮኞቹ በየለቱ ወደ መስክ እየተወሰዱ ከባድ የጉልበት ስራ እንዲሰሩ ይደረግ ነበር። አንድ ቀን ከእለቱ ስራ መጨረሻ በኋላ የምርኮኞቹ ጠባቂዎች አካፋዎችን ሲቆጥሩ አንድ አካፋ ጎድሎ ተገኘ። በዚያን ጊዜ ሞርኮኞቹን በሙሉ አሰልፈው፡ “አካፋውን የሰረቀው ማን ነው?” በማለት ጠየቁ። ማንም የሚናገር ጠፋ። ደግመው ጠየቁ አሁንም “እኔ ነኝ” ያለ አልነበረም። በዚህን ጊዜ አዛዡ “እንግዲያስ ሁላችሁም” ትገደላላችሁ አለ። ወዲያውኑ ዘበኞቹ ጠመንጃቸውን አቀባብለው በምርኮኞቹ ግንባር ላይ አነጣጠሩ። በቅጽበት ተስፋ ሁሉ ጨለመ። ሁሉም የጥይት አረር ለመቀበል ተዘጋጁ። ነገር ግን ቃታው ከመሳቡ በፊት አንድ ስኮትላንድዊ (Scottish) ወታደር ከሰልፉ ወደ ፊት ወጣ ብሎ “እኔ ነኝ አካፋውን የሰረቅኩት” አለ። ወዲያውኑ ዘበኞቹ ጥያት አዘነቡበትና ሞተ። ሌሎቹ ምርኮኞች የሟቹን አስከሪንና አካፎቹን ተሸክመው ወደ ካንፕ ተመለሱ። እንደደረሱም ጃፓኖቹ እንደገና አካፎቹን ቆጠሩ። የጠፋ አካፋ አልነበረም። ላካስ ቀድሞም ሲቆጥሩ ተሳስተው ኖሯል።፡ ያ ንጹህ ስኮትላንዳዊ ወታደር የጓዶቹን ሕይወት ለማትረፍ ብሎ የራሱን ሕይወት ሰጠ። ይህ ታሪክ ጌታ ኢየሱስ ለኛ ያደረገውን መስዋትነት ያስታውሰናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሚያስተምረን እኛ ሁላችን ከአዳም ከወረስነው ኃጢያት የተነሳ በበደላችን ሙታን የነበርንና ከተስፋ ርቀን ለዘላለም ሞት ፍርድ የተጠበቅን ነበርን። (ኤፌ. 2፡ 1-3) ነገር ግን በርሱ ሞት እኛ ሕይወትን እንድናገኝ ሃጢያት የሌለበት የእግዚአብዝሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ኃጢያት ሆኖ በመሞት እኛን ከሞት አዳነን። ወገኖቼ፦ ይሄ አስደናቂ ፍቅር ነው። ይሄ መስዋትነት ያለበት ፍቅር ነው። እግዚአብዝሔር ለኛ ያለውን ፍጹም ፍቅር የገለጸው እኛ ገና ሃጢያተኞች ሳለን ስለ እኛ ክርስቶስ በመስቀል እንዲሞት በመፍቀዱ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለኛ ነው። እርሱ ስለ እኛ በደልና መተላለፍ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብር ትቶ ወደ ምድር መጣ። አምላክ ሰው ሆኖ በሰውነት ደረጃ ወርዶ ራሱን አዋረደ። ኢሳያስ እንደተነበየው መልክና ውበት አልነበረውም፣ የተናቀ ከሰውም የተጠላ ሆነ። እርሱ ተጨነቀ፣ ተሰቃየ፣ እንደ በግ ታረደ። ለምን? ስለኛ። እኛ እንዳንሞት የኛን በደል ተሸክሞ ሞተ። እኛ በርሱ ቁስል፣ ስቃይና ሞት ተፈወስን። እኛ በርሱ ሞት ዳንን። ሞት የተገባን ሆኖ ሳለ አዳኛችን የኛን ሞት በመሞት ሕይወትን ሰጠን። ስለዚህ እኛ በጌታ ሞት ሕይወትን ያገኘን ሁሉ የፍቅር እዳ አለብን። በዚህ ሞት ያገኘነውን ክቡር ሕይወት መልሰን ለርሱ በመስጠት በሕይወታችን እርሱን ማክበር አለብን። ወዶናልና አዳነን።