top of page

ውደ እርሱ ብርሃን ተጠርተናል

“እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ።” (1 ጴጥ. 2፡9) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን “እግዚአብሔር እርሱ ብረሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም።” (1ዮሐ. 1፡5) ብርሃን የሕወት፣ የተስፋ፣ የእውቀት፣ የጽድቅ... ወዘተ ምልክት ነው። ጨለማ ደግም የሞት፣ የተስፋ መቁረጥ፣ የድንቁርና፣ የሃጢያት... ወዘተ ምልክት ነው። እግዚአብሔር ባለበት ሁሉ ያለው ሕይወት ነው፣ ተስፋ ነው፣ ጽድቅ ነው፣ መገለጥ ነው። እግዚአብሔር እርሱ ብርሃን ነው ደግምም በብርሃን ውስጥ ይኖራል። እግዚአብሔር እኛንም ወደ እርሱ ሲጠራን ወደ ራሱ ብርሃን ነው የጠራን። ይህ የእግዚአብሔር ብርሃን ወደ ሰዎች በክርስቶስ በኩል መጥቷል። ስለዚህ ጉዳይ ወንጌል ሲናገር “በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም” ይለናል። (ዮሐ. 1፡ 4-5) አህዛብ ሁላችን ያለ ክርስቶስ ተስፋ አጥተን በጨለማ የተቀመጥን ነበርን። ነገር ግን በጨላማ ተቀምጠን ለነበርነው ለኛ ታላቅ ብርሃን መጣልን። በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጥን ለኛ ብርሃን ወጣልን። ይህ በወንጌል ያገኘነው ብርሃን የእግዚአብሔር ብርሃን ነው። እግዚአብሔር በጨለማችን ላይ “ብርሃን ይብራ” ብሎ የልባችንን ጨለማ ገፎታል። እኛንም የብርሃን ልጆች አድርጎን ለአለም የምናበራ የአለም ብርሃን እንድሆን ሾሞናል። በወንጌል በማመን የእግዚአብሔርን ሕይወት ስንካፈል በእግዚአብሔር ብርሃን ውስጥ እንገባለን። በዚህ ብርሃን ውስጥ ስንሆን ሞት አያስፈራራንም። ይህ ብርሃን ባለበት ጨለማ ስፍራ የለውም። ብርሃኑ በጨለማ ይበራል። ይህ ብርሃን የሚዋጋንን ማንኛውንም የጨለማ ሃይል ይገልጣል። ብርሃኑ ሲገዛ ጨለማው ስፍራ ይለቃል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ብርሃንና ጨለማ አብረው ሊቆሙ አይችሉም። በእግዚአብሔር ብርሃን እየተመላለስን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ለመግባት አንችልም። በእግዚአብሔር ብርሃን ውስጥ እያለን በሃዝንና በትካዜ ውስጥ አንሰነብትም። ዳዊት እንደዘመረው እግዚአብሔር ብርሃናችን ሲሆን የሚያስፈራን፣ የሚያስደነግጠን አይኖርም። (መዝ. 27፡1) ወገኖቼ፦ እኛ ቀድም ጨለማ ነበርን አሁን ግን በጌታ ብርሃን ነን። (ኤፊ. 5፡8) ቀድም በሞት ጥላ ስር ነበርን አሁን ግን የዘላለም ሕይወት ተስፋ አለን። ቀድም ሙት ነበርን አሁን ግን ሕይወት አለን። ቀድም ያለ ክርስቶስ ነበርን አሁን ግን ክርስቶስ አለን። በዚህ የገና ሰሞን ለኛ የወጣውን ታላቅ ብርሃን እያሰብን እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page