ለማፍራት ስር መስደድ!
“በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፥ እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ።” (ኢሳ. 27፡6)
አንድ ታዋቂ የአገራችን ገጣሚ የዛፍ አስተዳደግን አስተውሎ የሚከተለውን ስንኝ ተቀኝቶኣል፦ ወደ ፊት ለማደግ እንሂድ ወደ ኋላ፣ እንደ ዛፍ እንደግ ዋርካ እንሁን ሾላ። በእርግጥም ልብ ብሎ ላስተዋለው ሰው የዛፍ አስተዳደግ ሁኔታ ትምህርት ሰጪ ነው። ዛፍ ጸንቶ ለመቆም፣ ወደ ላይ ለማደግና ለመስፋፋት፣ ለማበብም ብሎም ፍሬ ለማፍራት ስሮቹን ወደ ታች ይሰዳል። ስሮቹን የበለጠ ወደ ታች ወደ ምድር በሰደደ ቁጥር ለውሃና ለንጥረ-ነገር ሳይሰጋ አቋሙ፣ እድገቱና ፍሬያማነቱ አስተማማኝ ይሆናል። በ2017 የቤተ ክርስቲያችን መሪ ጥቅስ ከላይ ያሰፈርነው ነው። ጥቅሱ የያዕቆብን የመጪ ሁኔታ ሲገልጽ ከዛፍ አስተዳደግ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ምሳሌያዊ አገላለጽ ይጠቀማል። በመጀመሪያ ያዕቆብ ስር ይሰዳል። ከዚያም የተነሳ ማበብና ቅርንጫፍ ማውጣት ይሆንለታል። ይህ ደግሞ ፍሬ ወደ ማፍራት ያሸጋግረዋል። እንግዲህ ማበቡም ሆነ ቅርንጫፍ ማውጣቱና ፍሬያማ መሆኑ ስር የመስደዱ ውጤት ነው። በክርስትና ሕይወታችን ፍሬያማ እንድንሆን በቃሉና በመንፈሱ ስር መስደድ ያስፈልገናል። ስር መስደድ ቃሉን በጠለቀ መንገድ መረዳትን ያመለክታል። ስር መስደድ ቃሉን ማወቅና መስማት ብቻ ሳይሆን ቃሉንም ከራሳችን ጋር በእምነት አዋህደን መኖር ማለት ነው። ይህ ሲሆን ከውጪ የሚመጣውን ግፊ ለመቋቋም አቅም እናገኛለን። በቃሉ ላይ ስር ስዶ የታነጸ ሕይወት ንፋስና ማእበሉን ይቋቋማል። ስር መስደድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለ የጠነከረ ሕብረትን ይገልጻል። የውስጡ ሰው የሚጠነክረው ከመንፈስ ቅድስ ጋር ሕብረት ስናደርግ ነው። ከመንፈስ ቅድስ ጋር ያለን ሕብረት እየጨመረ የሚሄድ ሕብረት ነው። ከአንድ ደረኛ ወደ ሌላ ደረጃ ይሸጋገራል፤ ከክብር ወደ ክብር ያልፋል። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በህይወታችን እየጨመረ በሄደ ቁጥር፤ ሁልጊዜ በመንፈስ ስንመላለስ ስር እየሰደድን እንሄዳለን። ስር መስደድ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ መትጋትን ያሳያል። በሕብረት ማደግ ሌላው ስር የምንሰደበት አቅጣጫ ነው። እግዚአብሔር በሕብረት ውስጥ የከበረ በረከትን አድርጓል። በመንፈስ ሕብረት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ይሰራል። የክርስቶስን ፍቅር የመንካፈለው፤ የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ የምንበረታው ከወገኖች ጋር ባለ ሕብረት ነው። እግዚአብሔር ለቅዱሳን ያዘጋጀውን ሕይወትና በረከት የምንካፈለው በሕብረት ውስጥ ነው። ውሃ ያለ አሳ እንይሆን ክርስቲያንም ያለ ሕብረት አይሆንም። ወገኖቼ፦ በቃሉ፣ በመንፈሱና በሕብረት ስር ስንሰድ ጠንካራ የክርስትና አቋም ይኖረናል። እንደዚህ ስር ስንሰድ ልክ በውሃ ፈሳሾች አጠገብ የተተከለ ዛፍ ቅጠሉ እንደማይጠወልግና ፍሬውንም በየጊዜው እንደሚሰጥ እንዲሁ ሕይወታችን በእግዚአብሔር ደስታ የተሞላና ፍሬያማ ይሆናል። 2017 በእግዚብሔር ቃል ስር የምንሰድበት፣ በእግዚአብሔር ሞገስ የምናብብበት፣ በጸጋ የምንሰፋበት፣ በእግዚአብሔር መንፈስ የምናፈራበትና በተጽዕኖ የምንገለጥበት አመት ይሁንልን። መልካም አዲስ የበረከት አመት!