አምስቱ የአገልግሎት ስጦታዎች ፰ -- እረኞች
አምስቱ የአገልግሎት ስጦታዎች ፰ -- እረኞች
“እርሱም ... ሌሎቹም እረኞች... እንዲሆኑ ሰጠ።” (ኤፌ. 4፡ 11)
እረኛ ወይንም መጋቢ የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉም መንጋን የሚያግድ ወይንም የሚጠብቅ
ማለት ነው። ይህ ደግም አንድን ለመንጋ የሚያስፈልገውን ጥበቃና ጥንቃቄን የሚያደርገውን
አገልጋይ ይወክላል። ከመዝሙር 23 ላይ እንደምናስተውለው እረኛ ይመግባል፣ ይጠብቃል፣
ይመራል፣ ያሰማራል። በተጨማሪም በዮሐንስ 10፡11 ላይ እንደምናነበው ጌታ ኢየሱስ እራሱን
“መልካም እረኛ እኔ ነኝ” በማለት ገልጿል። ከክፍሉ እንደምንረዳው መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ
መንጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። መልካም እረኛ በጎቹን ለጠላት አሳልፎ አይሰጥም። ይልቁንም
ከተኩላውና ከበላተኛው እየተናጠቀ ያድናቸዋል። መንጎቹንም ፊት ቀድሞ ይመራቸዋል። በጎቹም
ድምጹን ያውቁታልና ይከተሉታል። እንግዲህ የእረኝነት አገልግሎት በጌታ ኢየሱስ እንደተገለጸው
አይነት የመልካም እረኛ አገልግሎት ነው።
እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አብም የእስራኤል እረኛ በሚል ምሳሌ
ተገልጿል። ኢሳያስ 40 ላይ እንደተጻፈልን እግዚአብሔር “መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥
ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።” (ቁ. 11) ከዚህ
ክፍል የእረኝነት አገልግሎት በብዙ ርሕራሔ እና የመንጋውን ሁኔታ እየተመለከቱ የሚከናውን
አገልግሎት እንደሆነ እንረዳለን። እረኛ መንጋውን እያስቸኮለ አይመራም። የሚሰማሩትን
ያሰማራል፣ ግልገሎቹን በብብቱ ይሸከማል፣ የደከሙትን ያበረታል፣ የሚያዝኑትን ያጽናናል።
በሌላም ስፍራ (ከሽማግሌዎች አገልግሎት ጋር በተያያዘ መልኩ) እንደምናነበው የእረኛ አገልግሎት
በክርስቶስ ኢየሱስ ደም የተዋጀችውን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ ነው።
እረኞች በዋናነት በአጢቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ መጋቢዎች ናቸው። አንዳንድ
ሰዎች የእረኞችን አገልግሎት በቀለበት ጣት ይመስሉታል። ምሳሌው እረኞች ከአጥቢያ ቤተ
ክርስቲያን ጋር ያላቸውን ቁርኝትና የአግለግሎታቸውን ማዕከል የት መሆን እንዳለበት
ያመለክታል። ልክ በትዳር ያሉ ወንድና ሴት ተጋቢዎች በቀለበት እንደሚተሳሰሩ ሁሉ እንደዚሁ
እረኛው ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ የተሰጠ ነው። በመሆኑም አገልግሎቱ እንደ ሌሎቹ ስጦታዎች
ተዘዋዋሪ ሳይሆን በዋናነት በአንድ ቤተ ክርስቲያን ያሉ ምእመናንን የመመገብ፣ የማሳደግ፣
የመንከባከብና የመምራት አገልግሎት ነው።