አምስቱ የአገልግሎት ስጦታዎች ፱ -- አስተማሪዎች
“እርሱም ... ሌሎቹም ... አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ።” (ኤፌ. 4፡ 11)
አስተማሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል በጥልቀት ለእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያስተምሩ
ናቸው። ከዚህም የተነሳ በቤተ ክርስቲያን ሚዛን የጠበቀ እድገት እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጾ
ያደርጋሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታምራትና በድንቆች እንዲሁም በትንቢት መንፈስ ያገለገለ
ሲሆን እንዲሁም ድንቅ አስተማሪም ነበር። ለዚህ ዋቢ ከተራራው ትምህርት የሚበልጥ የለም።
ማቴዎስ ይህንን ክፍል ሲጀምር “አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው” ይለናል። (ማቴ. 5፡2) እንዲሁም
ጌታችን በምሳሌ አፉን በመክፈት ሰዎች በሚገባቸው መልኩ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን
ያስተምር ነበር። እንዲሁም በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን አጵሎስ በማስተማር አገልግሎቱ የታወቀ
እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እርሱ በመጽሐፍት እውቀት የበረታ ነበር። እንዲሁም
በመንፈስ እየተቃጠለ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በትክክል ያስተምር ነበር። (ሐዋ. 18፡ 24-25) ስለዚም
አገልግሎቱ ማጠጣት (ማለትም የዳኑት የሚድጉበትን ቃል በማስተማር) ነበር። (1ቆሮ. 3፡6) የጌታ
ቤተ ክርስቲያን ወደ ሙላት እንድትመጣ ቅዱሳን በኃይልና በትንቢት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን
በትምህርትም መታነጽ ይኖርባቸዋል። ለዚህም ነው በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ነብያትና መምህራን
የነበሩት። ለመታነጽ ነብያትም አስተማሪዎችም (ሌሎቹም የአገልግሎት ስጦታዎች) ያስፈልጉናል።
አንድ የአገልግሎት ስጦታ ብቻውን በቤተ ክርቲያን የተሟላ እድገት አያመጣም።
የአስተማሪዎች ዋንኛው ብቃት የጌታን ትምህርት በትክክል መረዳትና ለሌሎች ግልጽ
በሆነ ሁኔታ ማስተማር ነው። ጌታ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጣቸው ትምህርት ነበር። ስለዚህም
የታላቁ ተልኮ ትዕዛዝ የጌታን ትምህርት ማስተማርን የሚጠቀልል ነው። (“እንግዲህ ሂዱና
አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ
እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ
ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28፡ 19-20)) ሐዋሪያቱም ያስተምሩ የነበረው ከጌታ
የተቀበሉትን ትምህርት ነበር። ስለዚህም ቃሉን የተቀበሉት በሐዋሪያት ትምህርት ይተጉ እንደነበር
ተጽፏል። (ሐዋ. 2፡42) ስለሆነም አስተማሪ አስቀድም ለራሱ የጌታን ትምህርት በትክክል መረዳት
ይኖርበታል። የትምህርት ስህተት በጣም አደገኛ ስለሆነ (እራስም ስቶ ሌሎችንም ለማሳት
ምክንያት ይሆናልና) አስተማሪ የትምህርቱን ትክክለኛነት እርግጠኛ መሆን ይጠበቅበታል።
ሌላው የአስተማሪዎች ብቃት የተረዱትን የቃል እውነት በሚገባ መልኩ ለሌሎች
ማስተላለፍ ነው። ስለዚህም ሐዋሪያው ጳውሎስ በመንፈስ ልጁ ለሆነው ለጢሞቲዎስ ሲጽፍለት
“ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ
ሰዎች አደራ ስጥ” ይለዋል። (2ጢሞ. 2፡2) መንፈሳዊ መረዳት አንድ ጉዳይ ሲሆን የተረዱትን
ማስተማር መቻል ደግም ሌላ ጉዳይ ነው። ጌታ አስተማሪዎችን ያብዛልን። አሜን።