top of page

አመስጋኞች እንሁን

“ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ" ይለናል።” (መዝ. 50፡23)

የምስጋና ከልብ የሚፈልቅ የአምልኮ መስዋዕት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምስጋና ሲናገር "ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ" ይለናል። (መዝ. 50፡23) በዚህ ቃል የምናስተውለው አንዱ ነጥብ ምስጋና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መስዋት እንደሆነ ነው። ምስጋና እግዚአብሔር በሕይወታችን ለሆኑት መልካም ነገሮች ማለትም ስላገኝናቸው በረከቶች፣ ሰለ አስደናቂ ጥበቃው፣ በኛ ላይ ስለበዛው ምህረቱ እና ወደር ስሌለው ፍቅሩ እያሰብን ሁሉ የሆነልን ከርሱ የተነሳ እንደሆነና የመልካምነት ሁሉ ምንጭ እርሱ እንደሆነ ተገንዝበን ለርሱ ብቻ የምናቀርበው (ለሌላ የማናጋራው) መስዋዕት ነው። የእግዚአብሔርን አባትነት እያሰብን ምስጋና ስናቀርብ ምስጋናችን በእግዚአብሔር ፊት መልካም መዓዛ ያለው መስዋዕት ይሆናል።

ምስጋና አንዱ እግዚአብሔርን የምናከብርበት መንገድ ነው። ለዚህ ነው ቃሉ ምስጋና የሚሰዋ ያከብረኛል የሚለው። በምስጋና ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ በሕይወታችን እግዚአብሔር የሰራውን ስራ እውቅና መስጠታችን ነው። አንድ ጊዜ አስር ለምጻሞች "ኢየሱስ ሆይ ማረን" እያሉ እየጮሁ ወደ ጌታ መጡ። (ሉቃ. 17፡12) ጌታም አስሩንም ፈወሳቸው። ከነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ "በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ።" (ቁ. 15) ጌታም "አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ?" በማለት ጠየቀ። ከአንዱም በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብር የተመለሰ አልነበረም። ብዙ ጊዜ ግን ከእግዚአብሔር ብዙ ነገር እንጠይቃለን፤ እርሱ ሲመልስልን ግን ለምስጋና አንገኝም። እንደ ዘጠኙ ለምጻምች በረከታችንን ተቀብለን ለበረከቱ ጌታ ምስጋና ማምጣትን እንዘነጋለን። ለተደረገልን ነገር እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባናል። ስናመሰግን እግዚአብሔርን እናከብራለን።

ምስጋና የእግዚአብሔርን ማዳን የምናይበት መንገድ ነው። እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ሰው ከድል ወደ ድል፤ ከበረከት ወደ በረከት ይሸጋጋራል። ከላይ በተመለከትነው ክፍል ውስጥ ዘጠኙ የተፈወሱት ለምጻሞች በረከታቸውን ይዘው ሄዱ። ከተቀበለው በረከት ይልቅ በፈወሰው ጌታ የተደነቀው አንዱ ግን ለማመስገን ተመለሰ። በታላው ድምጽ (ሰው ሁሉ እየሰማ) እግዚአብሔርን አመሰገነ። ይህም ብቻ አይደለም ጌታን እያመሰገነ በጌታ እግር ላይ በግንባሩ ወደቀ። ጌታም "ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው።" (ቁ. 19) ለዚህ ሰው የስጋ ፈውስ ብቻ ሳይሆን የነፍስ መዳን ሆነለት። በምስጋና የእግዚአብሔርን ማዳን አየ።

ወገኖቼ፦ ሁልጊዜ ስለሁሉ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል። ምስጋና በእግዚአብሔር ፊት የምናቀርበው መስዋዕት ነው። ምስጋና እግዚአብሔርን የምናከብርበት መንገድ ነው። ምስጋና የእግዚአብሔርን ማዳን የምናይበት ነው። አመስጋኞች እንሁን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page