top of page

በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናል።

“እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።” (ዮሐ. 1፡ 16-17)

በመካከላችን ሲያገለግለን የቆየው ወንድማችን ፓ/ር (ዶ/ር) ኃይሉ ቸርነት በአመት በዓል ሰሞን የሚያስታውሰን አንድ ቁም-ነገር ነበር። “እኛ አበሻ ክርስቲያኖች ድርብ ምጻተኞች ነን” ይላል። አባባሉን የሚጠቀምበት እንደ ክርስቲያኖች በምድር ስንኖር ምጻተኞች እንደሆንን ሁሉ ላለንበት አገርም እንግዳ መሆናችችን ለማመልከት ነው። ፓ/ር ኃይሉ በዓላትንም አስመልክቶ ሲናገር “እኛ አበሾች እድለኞች ነን ምክንያቱም ድርብ በዓል እናከብራለንና” ይላል። እነሆ አሁንም የፈረንጆቹን ገና አክብረን ዛሬ ደግሞ የአበሻውን ገና እናከብራለን። ለነገሩ ለኛ ገና (የጌታ ልደት) የየለቱ በአላችን ነው። በድጋሚ እንኳን ለብረሃነ ልደቱ አደረሳችሁ!

ሰዎች በገና ሰሞን ብዙ ስጦታ ይለዋወጣሉ። ገና የስጦታ በዓልም ተደርጎ ይወሰዳል። አሁን አሁን ንግድ በዛበት እንጂ የሃሳቡ መሰረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። ገና አብ የከበረውን ስጦታውን -- የሚወደውን አንድ ልጁን — ለአለም ሁሉ የሰጠበትን እለት በማሰብ የምናከብረው በዓል ነው። እግዚአብሔር ለምን አንድ ልጁን ሰጠን ብለን ስንጠይቅ መልሱ ስለሚወደን ነው። ዮሐንስ በወንጌል እንደ ጻፈልን “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐ. 3፡16) ልጁን ሲሰጠን በልጁ አምነን ሕይወት እንዲሆንልን ነው። በልጁ አምነን የእግዚአብሔር ሕይወት ተካፋዮች ስንሆን ደግሞ ወደ ተትረፈረፈ የጸጋ ሙላት ውስጥ እንገባለን። ለዚህም ነው መጽሐፍ በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናል የሚለን።

ጌታ ኢየሱስ ሲወለድ (መለኮት ስጋ ሲሆን) ጸጋና እውነትን ተሞልቶ ነው በመካከላችን ያደረው። እኛም በእምነት ከዚም ሙላት ተካፋዮች ሆንን። ከሙላቱ ተቀበልን። በመጀመሪያ የሕይወትን ስጦታ ተቀበልን። መጽሐፉ “በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች” ይለናል። (ዮሐ. 1፡4) ጌታ ኢየሱስ የመጣው ይህንን በርሱ ያለውን መለኮታዊ ሕይወት ሊያካፍለን ነው። ስለዚም በቃሉ “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ” ይለናል። (ዮሐ. 10፡10) በርሱ ያገኘነው ሕይወት የሚበዛና የተትረፈረፈ ሕይወት ነው። (“ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን።” ኤፌ. 2፡5) የተሰጠን ትልቁ ስጦታ ሕይወት ነው። ምክንያቱም ለሙት የሚያስፈልገው ፈውስ ሳይሆን ሕይወት ነውና። ይህ በክርስቶስ ያገኘነው ሕይወት ጨለማን ሁሉ የሚገፍ ብረሃንም ነው። የተቀበልነው የሕይወት ብርሃን በጨለማ ላይ ይበራል። ጨላማም አያሸንፈውም።

ከክርስቶስ ጋር የእግዚአብሔርን ሕይወት በመካፈላችን ደግም የእግዚአብሔር ልጅነት ማእረግ አገኘን። ዮሐንስ ይህንን ሲያበስረን “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” ይለናል። (የሐ. 1፡11-12) ልጆች በመሆናችን መንፈሱ ተሰጠን። (ሮሜ. 8፡15) በውስጣችን ያለው መንፈስ የሚረዳና የሚያበረታ፣ ልጅነታችንንም የሚመሰክር መንፈስ ነው። ልጆችም በመሆናች ደግሞ እግዚአብሔርን የምንወርስ ማለትም የመልኮትን ባህርይ የምንካፈል ሆነናል። ኢየሱስ ጸጋና እውነትን ተሞልቶ በመካከላችን መጣ። እኛ በርሱ በማመን በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀበልን። አሁንም በእምነት ወደ ጸጋው ዙፋን ስንቀርብ ሌላ ጸጋ እንቀበላለን። ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሁን። መልካም የገና በዓል ይሁንልን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page