top of page

ጸሎት አስተምረን -- መንግስት ለዘላለም የእግዚአብሔር ነው (ክፍል አስራ-ስድስት)

“እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን።” (ማቴ. 6፡13)

ከዚህ በፊት እንዳየነው በመንፈሳዊው አለም ሁለት መንግስታት አሉ። የእግዚአብሔር መንግስት አለ፤ የሰይጣን መንግስት አለ። በሉቃስ 12 ላይ እንደምናነበው ፈሪሳውያን ጌታን "በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ" አጋንንትን ያወጣል በማለት ከሰሱት። ጌታ ግን አሳባቸውን አውቆ "እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች ... ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?... እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።" (ቁ. 25፣ 26፣ 28) በዚህ ስፍራ በግልጽ እንደምናነበው ሰይጣን የሚሰራበት የጨለማ መንግስት አለ። ደግሞም የእግዚአብሔር ሃሳብ የሚከናወንበት የእግዚአብሔር መንግስት አለ። የሰይጣን መንግስት ከእግዚአብሔር መንግስት ተጻራሪ የሆነ የክፋት መንግስት ነው።

የመንግስታት ግንኙነት የኃይል ግንኙነት ነው። አንድ መንግስት ተጽንኦ በሚያሳድርበት ስፍራና ሁኔታ ሌላ መንግስት ተጽንኦ ማሳረፍ አይችልም። የእግዚአብሔር መንግስት በኃይል በምትሰራበት ስፍራ የጨለማው መንግስት መስራት አይችልም። የግዚአብሔር መንግስት የብርሃንና የጽድቅ መንግስት ስልሆነ የጨለማ ኃይል በፊቱ ሊቆም አይችልም። ስለዚህ የጌታ መንፈስ ባለበት ስፍራ ሁሉ አርነት አለ። ስለዚህ ነው የእግዚአብሔር መንግስት በምትገዛበት ስፍራ ሁሉ ሰዎች ከተለያየ እስራት የሚፈቱት። መንፈስ ቅዱስ በሚሰራበት ስፍራ የሚገለጠው የእግዚአብሔር መንግስት ነው። ጌታችን “እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች” ብሎናል። (ማቴ. 12፡28) አጋንንት ሰዎችን ለቀው የሚወጡት ከእነርሱ በሚበልጥ ኃይል ብቻ ነው። ያም ደግም የእግዚአብሔር መንግስት ኃይል ነው። ቤተ ክርስቲያን በምድር የእግዚአብሔር መንግስት መገለጫ ስለሆነች የገሃነብ ደጆች አይችሏትም። ያቆማትና የሚደግፋት ብርቱ የሆነው የእግዚአብሔር መንግስት ኃይል ነው።

የአባታችን ሆይ ጸሎት የሚፈጸመው መንግስት ለዘላለም የእግዚአብሔር እንደሆነ በማወጅ ነው። ምንም እንኳ አሁን በምንኖርበት አለም የተለዩ መንግስታት ቢኖሩም፤ እንዲሁም ምንም እንኳ አሁን በክፉ የሚገለጥ የጨለማ መንግስት ቢኖርም፤ መንግስት ግን ለዘላለም የእግዚአብሔር ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደሚያስተምረን በመጨረሻ “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፥ ለዘላለምም ትቆማለች።” (ዳን. 2፡ 44) በመጨረሻ ሰይጣንና መንግስቱ ከጭፍሮቹ ጋር በእሳት ባሕር ይጣላሉ። (ራዕ. 20፡10) አባታችን ሆይ መንግስት ለዘላለም ያንተ ብቻ ነው። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page