top of page

ተነሥቶአል!

“ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።” (ሉቃ. 24:5)

የክርስትናችን መሰረቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ስለተነሳ ነው ከማይጠፋ ዘር ሁለተኛ የተወለድነው እና የማያልፍ ርስት የተጠበቀልን። (1ጴጥ. 1:3-5) ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ስለተነሳ ነው የትንሳኤ ተስፋ ያለን። (1ቆሮ. 15:20) ኢየሱስ ክርስቶስ ስለተነሳ ነው የሞትና የሲዖል ኃይል የተሻረው። (ሮሜ 6:9) ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ስለተነሳ ነው ዳቢሎስ ድል የተነሳው። (ቆላ. 2:15) እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለተነሳ ነው መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር የመጣውና አሁን ከኛ ጋር ያለው። (ሐዋ. 2:33) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሓጢያትን ስርየት አገኘን፣ በትንሳኤው ደግሞ የክርስቶስን ሕይወት ተካፍለን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል።

የክርስቶስ ትንሳኤ በብዙ የማይታበል ማስረጃ የተረጋገጠ ነው። በሐዋ. 1:3 ላይ እንደምናነበው ጌታ “በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ” ራሱን ለደቀ መዛሙርቱ አሳያቸው። በአማርኛችን “ብዙ ማስረጃ” ተብሎ የተተርጎመው ቃል የማስረጃን ብዛት ብቻ ሳይሆን የሚያሳየው የማስረጃውንም የማይታበል መሆን ጭምር ነው። ስለዚህም በKing James Version ይህ ቃል “he shewed himself alive after his passion by many infallible proofs” ይላል። ቃሉ የማስረጃውን ብዛት “many” በሚለው ቃል ሲገልጽ፤ የማስረጃውን አይታበሌነት ደግሞ “infallible” በሚለው ቃል ይገልጸዋል። “Infallible” ለሚለው ቃል “Webster’s” የተሰኘው መዝገበ ቃላት እንዲህ የሚል ፍቺ ይሰጠዋል፡ “incapable of error (unerring); not liable to mislead, deceive, or disappoint (certain); incapable of error in de ning doctrines touching faith or morals.” እንግዲህ ዶክተር ሉቃስ በጥንቃቄ እንደጻፈልን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በብዙ ሊታበል በማይችል ጽኑ ማስረጃ የተረጋገጠ ነው።

የክርስቶስ ትንሳኤ በመላዕክት ምስክርነት ተረጋግጧል። መላዕክቱ ህያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። (ሉቃ. 24:5) የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በአይን ምስክሮች ተረጋግጧል። ጴጥሮስ በበዓለ-ሃምሳ ቀን ስብከቱ በአጽንዖት የመሰከረው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መነሳቱን ነው። ለተሰበሰቡት “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን” በማለት የአይን እማኝነቱን ሰጥቷል። (ሐዋ. 2፡ 32) በተጨማሪም አያሌ የአይን ምስክሮች ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን እንዳዩት ሐዋሪያው ጳውሎስ ጽፎልናል። (“መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል። 1ቆሮ. 15፡ 4-8) የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በታሪክም ተረጋግጧል። ለዚህም ነው ብዙዎች ሕይወታቸውን እስኪሰውለት ድረስ የተከተሉት። (ይቀጥላል)


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page