መንፈስ ቅዱስ — የተስፋው መንፈስ!
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳዔ ኃይል የሞትን ጣር አጥፍቶ ከተነሳና ካረገ በኋላ ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ ፈጸመው። ስለዚህም አሁን ባለንበት ዘመን ጌታ ኢየሱስ በክብር እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሙሽራይቱን ቤተ ክርስቲያንን እያዘጋጀ ከኛ ጋርና በኛ ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ስብእና (personality) ያለው አምላክ ነው። ከአብና ከወልድ ጋር ትክክል የሆነ ከስላሴ አንዱ ነው። መንፈስ ቅዱስ የኃይል መንፈስ እንጂ ኃይል ብቻ አይደለም። ጌታ ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን “እርሱ” እየለ በሰው መደብ ነው የገለጸው። (ዮሐ 14፡ 16-17፣25፣ 15፡26፣ 16፡ 5-15)መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ ነው። በፍጥረት ውስጥ ከአብና ከወልድ ጋር ተካፍሏል። (ዘፍ 1፡2) ልክ ዶሮ እንቁላሎቿን እንደምትታቀፍ የእግዚአብሔር መንፈስም በፍጥረት ጌዜ ባዶ የነበረውን ሊሞላ፣ ጭለማውን ሊገልጥ፣ ቅርጽ አልባ የነበረውን ቅርጽ ሊሰጥ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር። ይህም ስራው ዛሬም የቀጠለ ነው። ዛሬም መንፈስ ቅዱስ ይፈጥራል፣ ጭለማውን ይገልጣል፣ ባዶውን ይሞላል፣ ቅርጽ የሌለውን ቅርጽ ይሰጣል። እዮብ “የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጥሮኛል፤ ሁሉን የሚችለውም አምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጥቶኛል” (እዮብ 33፡4) እንዳለ የተፈጠርነው በእግዚአብሔር መንፈስ ነው።
መንፈስ ቅዱስ ስሜት አለው። በኤፌ 4፡30 ላይ “ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ” በማለት ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ይመክረናል። ክፍሉን ስንመለክተው የሚያንጽና የሚጠቅም ቃል እንጂ የማይረባ ቃል ከውስጣችን እንዳይወጣ ነው የሚያስተምረው። መራርነትን፣ ቁጣን፣ ንዴትን፣ ጭቅጭቅን፣ ስድብን፣ ክፋትን እንድናስወግድ ይነግረናል። ይቅር እንድንባባል ያሳስበናል። ይህ በማይሆንበት ቢዜ -- ይቅር መባባል ሳንችል ስንቀር፣ ረብ የለሽ ቃል ከኛ ሲወጣ፣ የስጋ ፍሬ ሲሰለጥንብን -- የታተምንበት መንፈስ ቅድስ (በውስጣችን ያለው) ያዝናል። ማዘን የስብእና ምልክት (የስሜት ምልክት) ነው። መንፈስ ቅዱስ የሚያዝነው ስለሚወደን ነው። ማዘን የፍቅር ቋንቋ ነው። የምትወዱት ሰው ቢበድላችሁ ታዝናላችሁ። መንፈስ ቅዱስ ስለሚወደን ስንበድለው ያዝናል።
መንፈስ ቅዱስ በአንድ ጌዜ ሁሉም ቦታ የሚገኝ ነው (He is Omnipresent) ከኛ ጋር ነው፣ በኛም ውስጥ ነው። አሁን በዚህ ሰአት በአለም ሁሉ አለ። መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ቻይ ነው (He is al- mighty) ጌታ የምድር አገልግሎቱን ያካሄደው በምንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቀብቶ ነበር። ጌታ ኢየሱስም ይህንኑ እውነት “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” (ሉቃ 4፡17) በማለት አረጋግጦልናል። ወገኖቼ፦ እኛም ለወንጌል ምስክሮች መሆን የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። መንፈስ ቅዱስ የሃይል፣ የፍቅርና ራስን የመግዛት መንፈስ ነው። መንፈስ ቅዱስን ሁልጌዜ “መንፈስ ቅዱስ ሆይ እንኳን ወደ ሕይወቴ፣ ወደ ቤቴ፣ ወደ አገልግሎቴ... ደህና መጣህ” እያልን እውቅና እየሰጠን እንቀበለው። አሜን።