ምስጉን ማን ነው?- አንድ
ምስጉን ማን ነው የሚለውን ጥያቄ ከማየታችን በፊት “ምስጉን” ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ “ምስጉን” የሚለውን ቃል ከሰው አንጻር“ብጽዕ” በሚል ተነጻጻሪ ቃል የተገለጸ ሲሆን ትርጉሙም “ደስተኛ የሆነ” ወይንም “የተባረከ” ወይም“ብሩክ” ማለት ነው። የእግግሊዘኛ አቻው ደግሞ “blessed” የሚለው ቃል ነው። (ማቴ. 5፡3-10፣ መዝ 1፡1) ምስጉን ማለት ከእግዚአብሔር አብሮነት የተነሳ ከእርሱ የሆነ ደስታ የተሰጠው ወይም ያለው ወይም ደግሞ በእግዜአብሔር የተባረከ ማለት ነው። እንኪያስ ምስጉን ማን ነው?
ምስጉን የሆነ ሰው ወይንም ህዝብ የእግዚአብሔርን ማዳን የቀመሰ ነው። ቃሉ ስለዚህ ሲናገር“እስራኤል ሆይ ምስጉን ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው?” (ዘዳ. 33፡29) ይላል። በእግዚአብሔር ማዳን ውስጥ ደስታ አለ። በዚህ ማዳን ውስጥ መጠበቅ አለ። “እርሱ የረድኤትህ ጋሻ” ነው ይለዋል። ጋሻ መመከቻና መጠበቂያ ነው። በማዳኑ ውስጥ እግዚአብሔር ለእስራኤል ጋሻ ሆኖለታል። ስለዚህም አስራኤል የጠላትን ፍላጻ አይፈራም። ፍላጻ ቢወረወርም አያገኘውም። ለእስራኤል እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ አስደናቂ የሆነ ጥበቃ አለበት። እስራኤልን የሚጠብቅ “አይተኛም አያንቀላፋምም።” (መዝ. 121፡4) በማዳኑ ውስጥ ደግሞ ሌላው ያለው ከፍተኝነት (excellence) ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር የእስራኤል የከፍተኛነት ሰይፍ ነው። ጋሻ ጥበቃን ሲያመለክት፤ ሰይፍ ደግሞ ኃይልን ያመለክታል። በእግዚአብሔር የዳነ ህዝብ ኃይሉ (ከፍታው) እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ከርሱ ጋር የሆነን ህዝብ የሚቋቋም የለም። ህዝቡ ከእርሱ ጋር ከሆነ እግዚአብሔር ለህዝቡ ይዋጋል። ከእግዚአብሔር ጋርም የሚዋጋ ሁሉ ይደቃል። የመውጊያውንም ብረት የሚቃወም ለእርሱ ይብስበታል።
እግዚአብሔር የህዝቡ ጋሻና ሰይፍ (መከታና ኃይል) ስለሆነ በእግዚአብሔር የዳነ ህዝብ በጠላቶቹ ላይ ብርቱ ነው። እንዲያውም ቃሉ እንደሚናገረው በእግዚአብሔር የዳነ ህዝብ ጠላቶቹ ይገዙለታል። መገዛትም ብቻ አይደለም በእግዚአብሔር የዳነ ህዝብ የጠላቶቹን ከፍታም ይረግጣል። ማለትም የግዚአብሔር ህዝብ ጠላቶች ከፍታ (የኃይላቸው ብርታት) በእግዚአብሔር ሕዝብ ፊት የሚረገጥ ነው። ለምን ቢባል እግዚአብሔር ላዳነው ሕዝቡ ኃይል ሰለሆነ ነው። እንዲያውም እግዚአብሔር የሕዝቡን ጠላቶች በሕዝቡ ፊት አውጥቶ “አጥፏቸው” ይላል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለውጊያ የሚልከው እርሱ ያሸነፈውን፣ የመታውን፣ የጣለውን ጥላት ያሳድድ ዘንድ ነው።
ወገኖቼ፦ ብጽዕና ወይም ባርኮት ማለትም “ምስጉን መሆን” ያለው በእግዚአብሔር ማዳን ውስጥ ነው። የእግዚአብሔርን ማዳን ያልቀመሰ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ምስጉን አይደለም። ቃሉ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” (ሮሜ 3፡23) እንደሚል በኃጢያት መስመር መጓዝ ከእግዚአብሔር ክብር መጉደል ነው። እግዚአብሔር ሲያድነን ወደ ክብሩ ይመልሰንና “ምስጉን”ያደርገናል። ይህም በእርሱ አብሮነት ውስጥ ያለውን ደስታ፣ ጥበቃና ኃይል እንድካፈል ያደርገናል። አሜን!