ምስጉን ማን ነው? — ሁለት
- Redeatu G. Kassa
- May 21, 2018
- 2 min read
ባለፈው ሳምንት እንዳየነው እግዚአብሔር ምስጉን የሚለው ሕዝብ በእርሱ የዳነውን ሕዝብ ነው። ስለዚህም ስለ ህዝቡ ሲናገር “እስራኤል ሆይ ምስጉን ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው?” (ዘዳ. 33፡29) ይለዋል። በእግዚአብሔር ማዳን ውስጥ የእርሱ ጥበቃና ቸርነትም እንዳለ አይተናል። ስለዚህ ማዳኑን የቀመሰ ምስጉን ሕዝብ ነው። ይህንን ሃሳብ ዛሬም ቀጥለን እናያለን።
መዝሙር እንድን ስናጠና እግዚአብሔር ምስጉን የሚለው ሰው ያለውን ባህርይ እንመለከታለን። መዝሙሩ “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ” (ቁ. 1) በማለት ይጀመራል። በዚህ ቁጥር የተዘረዘሩት እግዚአብሔር ምስጉን የሚለው ሰው የማያደርጋቸው ነገሮች ናቸው። ምስጉን አንደኛ በክፉዎች ምክር አይሄድም። ምክር አደገኛ ነገር ነው። ወይ ያፈርሳል ወይንም ይሰራል። በተለይ የክፉዎች ምክር ክፉ ነው። እንደ በልአም እና አኬጦፌል ያሉ ክፉ ምክርን የሚመክሩ አሉ። ምክራቸውን የተከተለ ወደ ክፋት ይሄዳል። ለዚህ ሃሳብ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ሮብአም የተባለው የእስራኤል ንጉስ ነው። የእስራኤል ሽማግሌዎች የአባትህን ቀንበር አቅልልን በለው ንጉሱን ጠየቁት። እርሱም በዚህ ጉዳይ ላይ ምክር ጠየቀ። ሽማግሌዎች “ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል” (1ነግ. 12:7)በማለት መከሩት። እርሱ ግን የሽማግሌዎቹን ምክር ችላ ብሎ ከርሱ ጋር ያደጉትን ብላቴኖች ምክር ጠየቀ። እነርሱም “ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች... አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው” (ቁ. 10-11) ብለው መከሩት። ንጉሱም ብላቴኖቹ እንደመከሩት ለህዝቡ መለሰ። ህዝቡም ተከፍቶ “በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም” (ቁ. 16) ብለው ወደ ድንኳኖቻቸው ተመለሱ። ይሁዳም ለብቻው ተነጠለ። የተቀረው እስራኤልም በላያችው ላይ ኢዮርብዓምን አነገሱ። ከዚህ ክፉ ምከር የተነሳ አገር ተከፈለ። ክፉ ምክር አይበጅም፤ ያፈርሳል። በክፉ ምክር ውስጥ የሚሰለጥነው የክፉ ሃሳብ ነው። ስለዚህ ምስጉን ሰው በክፉዎች ምክር አይሄድም። እንዲሁም ምስጉን ሰው በኃጢያተኞች መንገድ አይቆምም። ምስጉን ሰው ለሃጢያት የሚጋብዝን ሁኔታ ወደ ህይወቱ አያስገባም። አሁን የሃጢያተኞች መንገድ ሰፊ ነው። በኢንተርኔት የሚለቀቅ እርኩሰትን መለማመድ፣ ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ መሄድ፣ በማይገባን ስፍራ መገኘት በኃጢያት መንገድ መቆም ነው። ምስጉን ግን ይህንን አያደርግም። በሶስተኛ ደረጃ ምስጉን በዋዘኞች ወንበር አይቀመጥም። ዋዘኞች በእግዚአብሔር ነገር ይቀልዳሉ። መንፈሳዊውን እውነት ረብ እንደሌለው ይወስዳሉ። በጊዚያዊ ተድላና ጨዋታ ይወሰዳሉ። እግዚአብሔር ምስጉን የሚለው ሰው ግን እራሱን ከዚህ ይጠብቃል።
ወገኖቼ፦ እግዚአብሔር ምስጉን ይለናል። በልጁ ደም ቅድሶ አዲስ ህይወትን በመስጠት የተመሰጉኑና ክብር የሚገባቸው አድርጎናል። ነገር ግን ለዚህ ክብር የሚገባውን ህይወት መኖር ይጠበቅብናል። የክፉዎችን ምከር፣ የኃጢያተኞች መንገድና የዋዘኞችን ህበረት እናስወግድ። አሜን!
Recent Posts
See All“ተስፋን ቃል የሰጠዉ የታመነ ነዉና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ። (ዕብ 10፡ 23) ተስፋ ሰው በሕይወቱ እንደሚሆን በእርግጠኝነት የሚጠብቀው ነገር ነው። እያንዳንዱ ሰዉ ተስፋ የሚያደርገዉ...
ባለንበት ጊዜ በተለይም በ COVID 19 ወረርሽኝ የተነሳ በአብዛኛው ቤት ውስጥ ተከተን ባለንበት በዚህ ወቅት፤ የተለያየ ድምጽ፣ አስተሳሰብ፣ ጩኸት፣ አመለካከት እና ፕሮፓጋንዳ የምንሰማበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በተለይም...
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በምእራቡ አለምና በሃገራችን በኢትዮጲያ በተወሰነ መልኩ በትምህርት ቤቶች፣ በአንዳንድ ቢሮዎች፣ በቤትና በአፓርትመንት መስኮቶች ላይ በወረቀት የተቀለመ ህብረቀለማትን አዋህዶ የያዘ...
Comments