ልዩ መንፈስ -- ፈጽሞ መከተል!
- Redeatu G. Kassa
- Jun 2, 2018
- 1 min read
“ከእኔ ጋር የወጡ ወንድሞቼ ግን የሕዝቡን ልብ አቀለጡ፤ እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽሜ ተከተልሁ።” (ኢያሱ 14፡8)
የእግዚአብሔር ሰው ካሌብ ልዩ መንፈስ የነበረው ሰው ነው። ካሌብ የነበረው የልዩነት መንፈስ የእምነት መንፈስ ነው። ካሌብ በእግዚአብሔር ያመነ ብቻ ሳይሆን እግዚብሔርን ያመነ ሰው ነው። ይህ የልዩነት መንፈስ ደግሞ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ፈጽም የመደገፍ መንፈስም ነው። እንዲሁም ይህ ልዩ መንፈስ እግዚአብሔርን ፈጽም የመከተል መንፈስ ነው።
ካሌብ እግዚአብሔርን ፈጽም የተከተለ ሰው ነው። ይህንን ደግሞ ካሌብ እራሱ “እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽሜ ተከተልሁ” (ቁ. 8) በማለት ያረጋግጥልናል። ይህ ደግም ካሌብ ስለ ራሱ ምስክርነት እየሰጠበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት የተገለጠ ነበር። ካሌብ እግዚአብሔርን ፈጽም በመከተሉ የሚረግጠው ምድር ሁሉ ለእርሱና ለዘሩ ርስት እንደሚሆን ሙሴ መስክሯል። (ቁ. 9) ሙሴ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርም እራሱ ካሌብ ፈጽም እንደተከተለው መስክሮለታል። (ዘኁ. 32፡11-12፤ ዘዳ. 1፡36) ከዚህም የተነሳ ትውልዱ ሁሉ በምድረበዳ ሲቀር ካሌብ ግን በሕይወት ቆይቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ገባ። ኬብሮንንም ርስት አድርጎ ወሰደ። (ቁ. 14)
ካሌብ እግዚአብሔርን ፈጽም ነበር የተከተለው። እግዚአብሔርን የተከተለው በሙሉ ልቡ ነበር። ሁለንተናውን ለእግዚአብሔር የሰጠ ሰው ነው። ካሌብ ያልፍበት የነበረው ሁኔታና አካባቢው ልብን ሊከፍሉና ማመንታት ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ነበሩ። እርሱ ግን ከአስሩ ወገኖቹ ጋር ለአሰሳ በወጣ ጊዜ የተሰለፈው ከብዙሃኑ ሃሳብ ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ሃሳብ ጋር ነበር። አብረውት የወጡት አስሩን አልተከተለም። እንዲሁም ተስፋ የቆረጠውንም ሕዝብ አልተከተለም። እርሱ እግዚአብሔርን ተከተለ።
መከተል የራስን ሃሳብ በእግዚአብሔር ሃሳብ መጠቅለልን የሚጠይቅ ነው። በፈቃዱ ውስጥ መግባትን ይጠይቃል። ጌታችንም በወንጌላት ያስተማረን “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ነው። (ማቴ. 16፡24) የተጠራነው ጌታን እንድከተል ነው። የራሳችንን ፈቃድ እያገለገልን ጌታን ለመከተል አንችልም። መከተል መስቀልንም መሸከም ይጠይቃል። ነገር ግን ጌታን በፍጹም ልብ ስንከተል እንደ ካሌብ ከመልካም ነገር አንጎድልም። በህይወት እንኖራለን፤ ርስታችንን እንወርሳለን፤ በተስፋው ቃል ላይ እንደገፋለን፤ ሽምግልናችን በዘይት ይለመልማል። ወገኖቼ፦ በተሰጠን ዘመን ልክ እንደ ዳዊት የእግዚአብሔር ሃሳብ እንድናገለግል እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!
Recent Posts
See All“ተስፋን ቃል የሰጠዉ የታመነ ነዉና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ። (ዕብ 10፡ 23) ተስፋ ሰው በሕይወቱ እንደሚሆን በእርግጠኝነት የሚጠብቀው ነገር ነው። እያንዳንዱ ሰዉ ተስፋ የሚያደርገዉ...
ባለንበት ጊዜ በተለይም በ COVID 19 ወረርሽኝ የተነሳ በአብዛኛው ቤት ውስጥ ተከተን ባለንበት በዚህ ወቅት፤ የተለያየ ድምጽ፣ አስተሳሰብ፣ ጩኸት፣ አመለካከት እና ፕሮፓጋንዳ የምንሰማበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በተለይም...
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በምእራቡ አለምና በሃገራችን በኢትዮጲያ በተወሰነ መልኩ በትምህርት ቤቶች፣ በአንዳንድ ቢሮዎች፣ በቤትና በአፓርትመንት መስኮቶች ላይ በወረቀት የተቀለመ ህብረቀለማትን አዋህዶ የያዘ...
Comments