top of page

አምልኮ -- በመንፈስና በእውነት ማምለክ (ሁለት)

ባለፈው ሳምንት እንዳየነው የሰማሪያቷ ሴት ከነበራት መንፈሳዊ ጥያቄ ዋንኛው የአምልኮ ጥያቄ ነበር። ምድንድን ነው ማምለክ? የት ነው የሚመለከው -- በተቀደሰ ተራራ ነው ወይንስ በቅድስቲቱ ኢየሩሳሌም፣ እንዴት ነው የሚመለከው? የሚሉ ጥያቄዎች ነበራት። አምልኮ እግዚአብሔርን ከመውደድ ተነስተን ብሕይወታችን ለእርሱ የምንሰጠው ስፍራ እንደሆነ አይተናል። በሕይወታችን እግዚአብሔር አንደኛ ሌላው ሁሉ ተከታይ ከሆነ እግዚአብሔርን እያመለክን ነው።

የሰማሪያቷ ሴት ዋንኛ የምልኮ ጥያቄ እግዚአብሔር የት ነው የሚመለከው የሚል ነበር። አይሁዶች ለእግዚአብሔር ለመስገድ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። ሰማሪያውያን ደግሞ እግዚአብሔር እነርሱ ቅዱስ በሚሉት በገሪዛን ተራራ ይመለካል ይሉ ነበር። አይሁድም ሆኑ ሰማሪያን አምልኮን የተረዱበት መንገድ ውስን ነበር። ጌታ ግን ለሴቲቱ እንዲህ አላት፦ “አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል።” (ዮሐ. 4፡ 21) አምልኮ ስፍራ ተወስኖለት በተወሰነ ጊዜ የሚከናወን አይደለም። አምልኮ በይትኛውም ስፍራ፣ በየትኛውም ሁኔታ ይከናወናል። የምናደርገውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ካደረግነው አምልኮ ነው። ስራችንን ስንሰራ እግዚአብሔርን እያሰብን እርሱን ደስ ለማሰኘት ከሰራን አምልኮ ነው። ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት እግዚአብሔር በመፍራትና በማክበር ከሆነ አምልኮ ነው። ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር ተነስተን ሌሎችን ስንወድ አምልኮ ነው። ለዚህ ነው ቃሉ “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” የሚለን። (ቆላ. 3:17)

ጌታ እንዳስተማረን እግዚአብሔር የሚመልከው በመንፈስና በእውነት ነው። ለሴቱቱ እንዲህ አላት፦ “ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና” (ቁ. 23)። እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ በየትኛውም ስፍራ ይገኛል። ስለሆነም ዋናው ጥያቄ እግዚአብሔር የት ነው የሚመለከው ሳይሆን እንዴት ነው የሚመለከው የሚል መሆን አለበት። እግዚአብሔር የሚወደውና የሚቀበለው አምልኮ በመንፈስና በእውነት የሆነን አምልኮ ነው። ሁለቱ የአምልኮ መሰረቶች እግዚአብሔርን በእውነት ማምለክ እና እግዚአብሔርን በመንፈስ ማምለክ ናቸው። በእውነት ላይ ካልቆምን ወደ እግዚአብሔር ልንደርስ አንችልም። እውነት ክርስቶስ ነው። (ዮሐ. 1:16) ወደ አለም የመጣውም እውነተኛ ብረሃን ክርስቶስ ነው። (ዮሐ. 1:9) በመካከላችንም ያደረው ጸጋና እውነትን ተሞልቶ ነው። (ዮሐ. 1:14) እውነትም በእርሱ እንዳለ እናውቃለን። (ኤፊ. 4:21) እግዚአብሔር የሚቀበለውን አምልኮ ለማቅረብ አስቀድመን በክርስቶስ መሆን አለብን። እግዚአብሔር ደስ የተሰኘው በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ነው። እኛንም የሚቀበለን በልጁ በኩል ነው። እግዚአብሔርንም ለማምልክ በልጁ በኩል መቅረብ አለብን።

ሌላው መሰረታዊ ነጥብ እግዚአብሔር መንፈስ ነውና ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኘው በመንፈሳችን በኩል ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ መንፈሳችንን ሕያው አድርጎ እግዚአብሔርን እንድናመለክ ያስችለናል። ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ እግዚአብሔርን ለማምለክ አንችልም። መንፈስ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ይገልጥልናል። መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ፍቅር በልባችን ያፈሳል። መንፈስ ቅዱስ በመንፈሳችን ወደ እግዚአብሔር እንድቀርብ ያስችለናል። ወገኖቼ፦ እግዚአብሔርን ማምለክ ማለት እውነት የሆነውን ክርስቶስን ወደ ህይወታችን ጋብዘን በዛ ሕይወት ትኩስነት እየተመላለስን መንፈስ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር በሚሰጠን መገለጥ ለእርሱ መኖር፣ ለእርሱ መገዛት፣ እርሱን ማወደስ፣ ለእርሱ ክብር መስጠት፣ እርሱን ማመስገንና በእርሱ ደስ መሰኘት ነው። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page