top of page

ይከናወንልሃል

“ነገር ግን ጽና እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ህግ ሁሉ ጠብቅ፣ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደግራም አትበል። የዚህ ህግ መጽሃፍ ከአፍህ አይለይ፣ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በለሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜ መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።” (ኢያሱ 1፣ 7-8)

ስኬትና መከናወን የሁሉ ሰው ዋነኛ ፍላጎት ነው። ሁሉም ኑሮው እንዲቃናለትና እንዲከናወንለት የማይምሰው ጉድጓድና የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ከላይ በተጠቀሰው የመጽሃፍ ክፍል ግን ከእግዚአብሄር ዘንድ የሆነው ስኬትና መከናወን የሚገኝበትን መንገድ እራሱ እግዚአብሄር ለኢያሱ ሲያስተምረው እንመለከታለን።

ወቅቱ እስራኤልን ከግብጽ ያወጣው ሙሴ የተሰጠውን የአገልግሎት ድርሻ ከተወጣ በኋላ ያንቀላፋበትና በተራው ደግሞ ኢያሱ የተስፋውን ምድር ለህዝቡ የማውረስን ሃላፊነት የተቀበለበት ነበር። የተሰጠው ሃላፊነት ግን ኢያሱን የከበደውና ያስፈራው ስለነበር እግዚአብሄር ካጠገቡ ሆኖ ሲያጽናናውና ሲያበረታታው እናያልን። በተጨማሪም፣ በተሰጠው ኃላፊነትና ራዕይ የተቃናለትና የተከናወነለት ይሆን ዘንድ ይሄድባቸው የሚገቡትን መርሆዎች ያስቀምጥለታል።

ከነዚህም መርሆዎች ዋነኛው “ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሁሉ ጠብቀው፣ አድርገውም” የሚለው ነው። ይህ ለቃሉ የመታዘዝን መንገድ የሚያመለክት ሲሆንና አስቀድሞ ግን የሚታዘዙትን ቃል መሞላትና መማርን የሚጠይቅ ነው። ያልተሞላነውንና ያልተማርነውን ቃልማ ከየት አምጥተን ልንታዘዘውና ልንጠብቀው ይቻለናል? ኢያሱ ግን ዘወትር ከሙሴ አጠገብ የማይጠፋ ስለነበረና ሙሴ ያስተምር የነበረውን ቃል ሲማርና ሲሞላ የኖረ ስለነበር፣ እግዚአብሄርም የኢያሱን የቃል መሞላት ስለሚያውቅ ይህን የተሞላውን ቃል እንዲጠብቀውና እንዲያደርገውም አዘዘው። እንግዲህ በዚህ ባለንበት ምድር፣ ዘመንና ህይወት እግዚአብሄር እንድናከናውነው በውስጣችን ባስቀመጠው ራዕይና ሃላፊነት፣ ማለትም በአገልግሎት፣ በንግድ ቢሆን በግብርና፣ በሌሎችም ተግባራት ከእግዚአብሄር ዘንድ መቃናትና መከናወን ይሆንልን ዘንድ አስቀድመን በእግዚአብሄር ቃል መሞላትና የተሞላነውን ቃል ደግሞ እንድንኖረውና እንድንጠብቀው ይመክራል።

ሌላው እግዚአብሄር ለኢያሱ የሰጠው መርህ ደግሞ መጠበቅና ማድረግ የሚችልበትን መንገድ ነው። እርግጥ ነው፣ ልክ እንደእግዚአብሄር ቃል መኖርና ቃሉን መጠበቅ ለአንድ አማኝ እጅግ የሚያስቸግር ነው:: ነገር ግን እግዚአብሄር ለኢያሱ ቃሉን ሊጠብቅና ሊታዘዘው የሚችልበትን መንገድ ሲያስተምረው “ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንና በሌሊት አስበው” በማለት ነበር። ሰው ብዙ ጊዜ አንድን ነገር ለማድረግ ሲያስብ አስቀድሞ ስለሚያደርገው ነገር ደጋግሞ ያሰላስለዋል፣ በመቀጠልም ያሰላሰለውን ነገር ይሆነዋል ወይንም ይፈጽመዋል። ለምሳሌ ነጋዴ ለመሆን የሚፈልግ ሰው አስቀድመው ስለሚነግደው ነገር፣ ቦታውን፣ አዋጪነቱን፣ የገንዘቡን መጠን፣ ወዘተ.... ቀንም ሌሊትም ያሰላስላል፣ አንድ ቀንም እራሱን ነጋዴ ሆኖ ያገኘዋል። ልክ እንደዚሁ የእግዚአብሄርንም ቃል በቀንና በሌሊት የሚያሰላስል ሰው ራሱን በቃሉ በተቃኘ ህይወት ውስጥ ሆኖ ያገኘዋል — የተሞላነውን ቃል ዘወትር ማሰላሰሉ ለስኬት ያበቃል።

በመጨረሻም “ለኢያሱ የተነገረው የዚህ ሕግ ቃል ከአፍህ አይለይ” የሚል ነው። ጌታችን ኢየሱስ በአንድ ወቅት “ሰው በልቡ ሞልቶ ከተረፈው በአፉ ይናገራል” እንዳለው ቃሉን ደግሞ ዘውትር በልባችን የምናሰላስለው ከሆነ ሁል ጊዜ በየትኛውም ጉዳይ ስንናገር ከአፋችን የሚወጣው የእግዚአብሄር ቃል ይሆናል ማለት ነው። ዘወትር ደግሞ እግዚአብሄር በመጽሃፍ የጻፈልንን ተስፋና የድልን ቃል የምናውጅ ከሆነ የምናገረው በእግዚአብሄር ቃል የተመሰረተ የእምነት ቃል ለስኬት ያበቃናል። ኢያሱ ደግሞ ከልጅነቱ ጀምሮ አንደበቱ የእምነትን ቃል የሚናገርና የአፉም ቃል ለስኬት እንዳበቃው በሙሴ አማካኝነት ለስለላ በተላከበት ወቅት ካመጣው ሪፖርት ማወቅ ይቻላል። በመሆኑም ለኢያሱ እንደተሰጠው እንደእግዚአብሄር መርህ መሰረት ከእግዚአብሄር ዘንድ ለሆነ ስኬትና መከናወን የሚያበቃው እንደእግዚአብሄር ቃል መኖር ሲሆን፣ ቃሉን ለመጠበቅና ለማድረግ ደግሞ በቃሉ መሞላት፣ የተሞላነውን ቃል በቀንና በሌሊት ማሰላሰልና፣ በውስጣችን የምናሰላስለውን ቃል ደግሞ በሁሉ ስፍራ በአፋችን ማወጅ እንደሆነ ክፍሉ ያስተምረናል።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page