top of page

ኢያሱ -- በእግዚአብሔር ፊት የማይታጣ አገልጋይ

“ሙሴም ድንኳኑን እየወሰደ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ ከሰፈሩም ራቅ ያደርገው ነበር፤ የመገናኛውም ድንኳን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርንም የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበር... ነገር ግን ሎሌው ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር።” (ዘጸ. 33፡ 7፣11)

የሙሴ ሎሌ የነበረው ኢያሱ እጅግ ብዙ አስደሳች የሕይወት ልቀቶች የነበሩት የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው። ኢያሱ እስራኤል ከአማሌቅ ጋር ሲዋጋ የእስራኤልን ጦር የመራ ብርቱ የጦር ጀኔራል ነው። ሙሴ ከንዓንን እንዲሰልሉ ከላካቸው 12 የነገድ አለቆች መካከል አንዱ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሃሳብ ተርድቶ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ገብቶ መውረስ እንዲሚችል የእመነትን አዋጅ ከተናገርው ከካሌብ ጋር አብሮ የቆመ ብቸኛ መሪ ነው። ደግሞም እስራኤልን መርቶ ነገስታትን ድል ነስቶ ህዝቡን በድል የተስፋይቱን ምድር ያወረሰ ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የኢያሱን ሕይወት መልካም አርአያ የሚያደርገው ትልቁ ነገር ኢያሱ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት መገኘቱና እግዚአብሔርን ሁልጊዜ መፈለጉ ነው።

ኢያሱ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ሰው ነበር። ከላይ በሰፈረው ክፍል እንደተገለጸው የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ የመገናኛውን ድንኳን ከሰፈር ውጭ፣ ከሰፈሩም ራቅ አድርጎ ይተክለው ነበር። እግዚአብሔርንም የሚፈልግ ሰው ከሰፈር ወጥቶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይሄድ ነበር። የመገናኛው ድንኳን የእግዚአብሔር መገኘትና ክብሩ የሚገለጥበት ስፍራ ነው። ስለዚህም እግዚአብሔር ለማግኘት የሚፈልግ ሰው ከሰፈር ወጥቶ ወደ ድንኳኑ ይሄዳል። በዚያም የአምልኮ ስርአትን ይፈጽማል። ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ሲሄድ ግን የተለየ ነገር ይሆናል። እስራዔላዊያን ሙሴ ከሰፈሩ ተነስቶ ወደ መገናኛው ድንኳን እሲኪገባ ድረስ በሩቅ ሆነው የመለከቱታል። ሙሴ ወደ ድንኳኑ ሲገባ የዳመና አምድ በድንኳኑ ደጃፍ ይቆማል። ሕዝቡን ያንን የእግዚአብሔርን ክብርና መገኘት ሲመለከት እያንዳንዱ እግዚአብሔርን በማክበር ይሰግዳል። የእግዚአብሔር ድምጽም ወደ ሙሴ በግልጽ ይመጣል። ሙሴም በመገናኛው ድንኳን ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋግሮ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል። ኢያሱ ግን ክብሩና መገኘቱ ካለበት ከድንኳኑ ምንጊዜም አይለይም። ውሎውና አዳሩ በመገኘቱና በክብሩ ውስጥ ነበር። ሰፈርተኛው ከሩቅ አይቶ ሲሰግድ እርሱ ግን ተገኝቶ ያመልክ ነበር። ሰው እግዚአብሔርን ሲፈልግ ወደ መገናኛው ድንኳን ሲወጣ ኢያሱ ግን ጉዳይ ኖረውም አልኖረውም ከመገናኛው ድንኳኑ አይታጣም ነበር።

የኢያሱን ሕይወትና አገልግሎት ስኬታማ ያደረገው ዋንኛው ነገር በእግዚአብሔር ፊት አለመታጣቱ ይመስለኛል። ኢያሱ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን እየፈለገ፤ እርሱም ደግሞ እየተገኘለት በክብር ኖሮ ያለፈ ታላቅ የእምነት አርበኛ ነው። የሱ ሕይወት ዛሬ ለኛ ትልቅ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው። እግዚአብሔርን የምንፈልገው እንደ ባለ ጉዳይ ጉዳያችን ሲጎድል ብቻ ነው ወይንስ ሁልጊዜ እንፈልገዋለን። በማንኛውም ሁኔታ እርሱን ለመፈለግ እንተጋ ይሆን?


Recent Posts
Archive
Search By Tags
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
spotify-badge-button-listen-wh-BG.png
apple-podcasts-logo.jpg
Google-Podcasts-Badge.jpg
RadioPublicc.png
breaker.png
pocketcasts3.png
Anchor-Podcast-Logo.png

 

5850 N. Elston Avenue 

Chicago, Il 60646

10:00 AM TO 12:00 PM SUNDAY

7:00PM TO 9:00PM FRIDAY

  • Facebook Social Icon
  • Twitter Social Icon
  • Google+ Social Icon
  • YouTube Social  Icon
bottom of page