top of page

ኢያሱ -- የእምነት አርበኛ

“...ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ... ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት። እግዚአብሔርስ

ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል። ነገር ግን

በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው

ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው ተናገሩአቸው።” (ዘኁ. 16:6-9)

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ኢያሱ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈልግና እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር

የሆነ አገልጋይ እንደሆነ አይተናል። ሌላው የኢያሱ መለያ ልክ እንደ ካሌብ በእግዚአብሔር ላይ ጽኑ እምነት

ያለው መሪ መሆኑ ነው።

እግዚአብሔር ወደ ሰው ተመልክቶ የሚደሰትበት አንዱ ነገር እምነት ነው። ሰውንም የሚነቅፍበት

ነገር ቢኖር የእምነት መጉደል ነው። በተለይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ከነበረው አገልግሎት

ይህንን በሚገባ እንረዳለን። በሉቃስ 7 ላይ የምናገኘው የቅፍርናሆም መቶ አለቃ ኢየሱስን ያስደነቀው

በእምነቱ ነበር። የመቶ አለቃው “ቃል ተናገር ብላቴናዬም ይፈወሳል” አለ። (ቁ. 7) የመቶ አለቃው የኢየሱስ

ቃል ስልጣን እንዳለው፣ ኢየሱስ ከተናገረ የማይሰማ ፍጥረት እንደሌለ አማኖ ነበር። ኢየሱስ በእምነቱ

ተደነቀ። ከአስራ ሁለት አመት ጀምሮ ደም ይፈሳት የነበረችውና የኢየሱስን የልብሱን ጫፍ የዳሳስኩ

እንደሆን እፈወሳላሁ ያለችውንም ሴት ጌታ ከስቃይዋ የገላገላት ስለ እመነትዋ ጥንካሬ ነው። ጌታ “ልጄ

ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። (ማቴ. 9:22) ሴቲቱም ወዲያውኑ ዳነች። ጌታ ሐዋሪያቱን

ገስጿቸው የነበረው ስለ እምነታቸው መጉደል ነበር። (ማቴ. 6:30፤ 8:26) ጴጥሮስንም እንዲሁ የገሰጸው

እምነት ስለጎደለውና ሰለ መጠራጠሩ ነበር። (ማቴ. 11:31) ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው እግዚአብሔር

እንዳለ፤ ለሚፈልጉትም ዋጋን እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል። (ዕብ. 11:6) በማንኛውም ሁኔታ

ብንሆንም በዚህም ውስጥ እግዚአብሔር አለ የሚል እምነት ከሁኔታዎች በላይ ያደርገናል። እምነት ደግሞ

ከግዚአብሔር ዘንድ ዋጋን ያስገኝልናል።

ኢያሱና ካሌብ የተለየ እምነት የነበራቸው መሪዎች ነበሩ። አብረዋቸው ለስለላ የወጡት የነገድ

አለቆች አይኖቻቸው በጠላቶቻቸው ጉዙፍነት ላይ አርፎ የሕዝቡን ልብ ሲያቀልጡ፤ ኢያሱና ካሌብ ግን

ጠላቶቻቸውን በእግዚአብሔር ትልቅነት አይን አይተው የእምነትን ቃል ተናገሩ። ለኢያሱና ለካሌብ

የመውረስ እና ያለመውረስ ጉዳይ በምድሪቱ በሰፈሩት ሕዝቦች ሁኔታ የተመሰረተ ሳይሆን እነርሱ

ከእግዚአብሔር ጋር ካላቸው ሕብረት ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ገብቷቸዋል። “እግዚአብሔር ከወደደን” ወደ

ምድሪቱ ያገባናል፣ ምድሪቱንም ይሰጠናል አሉ። ለእነርሱ ጉዳዩ ብርታታቸው ወይንም የጠላቶቻቸው

ጥንካሬ ሳይሆን እግዚአብሔር ነበር። የምድሪቱንም ሰዎች አይተው ልባቸው እንደ ሌሎቹ ወንድሞቻቸው

አልደነገጠም። ይልቁንም “በእግዚአብሔር ላይ አታምጹ” ሲሉ ሕዝቡን ገሰጹ። አለማመን አመጽ ነው።

አለማመን የእግዚአብሔርን ኤልሻዳይነት አለመቀበል ነው። ኢያሱና ካሌብ አስቀደመው እግዚአብሔርን

አይተው ቀጥለው ጠላቶቻቸውን ሲያዩ፤ ጠላቶቻቸው እንደ እንበጣ የሆኑ፣ ጥላቸው ከላያቸው ላይ

ይተገፈፈ ሆነው ታዩአቸው። የሚያስፈሩና የሚባሉ ሆነው ሳይሆን የታይዋቸው የፈሩና የደነገጡ፣ እንደ

እንጀራ የሚበሉ ሆነው ነበር የታዩአቸው። ሌሎቹ ግን አስቀደመው እግዚአብሔርን ሳያዩ ጠላቶቻቸውን

ስላዩ የታያቸው የአምላካቸው ትልቅነት ሳይሆን የጠላቶቻቸው ግዝፈት ነበር። ወገኖቼ፦ እኛም

በችግሮቻችን ላይ ከምናተኩር ይልቅ የአምላካችንን ትልቅነት እንይ። ያን ጊዜ ችግራችን ያንሳል። አሜን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page