top of page

ምናሴና ኤፍሬም ያደረገልን እግዚአብሔር ይመስገን።

“ዮሴፍም የበኵር ልጁን ስም ምናሴ ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል፦ እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ የአባቴንም ቤት አስረሳኝ፤ የሁለተኛውንም ስም ኤፍሬም ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል፦ እግዚአብሔር በመከራዬ አገር አፈራኝ።” “(ዘፍ. 41:51-51)

ዮሴፍ ከግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ተስፋን የተቀበለ ሰው ቢሆንም በብዙ መከራ ውስጥ አልፏል። ወንድሞቹ ጠሉት። ከዚያም አልፎ እንዲሞት ብለው በጉድጓድ ውስጥ ጣሉት። ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲሞት አልፈቀደምና በወንድሞቹ ምክንያት ለባርነት ተሽጦ ወደ ግብጽ ወረደ። በባርነት ምድርም ባልሰራው ወንጀል ተከሶ በግፍ ወደ ወህኒ ቤት ተጋዘ። ቃሉ እንዲሚለን“እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፥ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ። ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ፥ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው።” (መዝ. 105፡ 18-19) ይሁንና እያንዳንዱ ዮሴፍ ያለፈበት መከራ የበለጠ እግዚአብሔር ወዳየለት ፍጻሜ እያስጠጋው ነበር።

ምንም እንኳ ዮሴፍ በጣም አዳጋች በሆነ የሕይወት መስመር ውስጥ ያለፈ ቢሆንም የእግዚአብሔር ህልውና ግን አንድም ጊዜ አልተለየውም። ዮሴፍ በወንድሞቹ በጉድጓድ ውስጥ ሲጣል እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር። ዮሴፍ በጶጢፋራ ቤት ሲያገለግል እግዚአብሔር ከእርሱ ጋራ ነበርና የሚሰራው ሁሉ ይከናወንለትና ይቃናለት ነበር። ከዚህም የተነሳ በአሰሪው ፊት ሞገስ ነበረው። ዮሴፍ በግፍ እስር ቤት በተጣለም ጊዜ እግዚአብሔር አብሮት ነበር። ቃሉ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይለናል፡ “እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው።” (ዘፍ. 39:21) ስለዚህም አንድም ጊዜ ዮሴፍ ስለሚያልፍበት ሁኔታ ሲያማርር አንመለከትም። እንዲያውም በዚያ ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔር የሰራውን በጎነት እያሰበ በታላቅ የምሕረት ልብ ተሞቶ ነበር። በተለይም ለጥፋትና ለሞት የሸጡትን ወንድሞቹን ሲያገኝ ከአንደበቱ የወጣው የቁጣና የበቀል ቃል ሳይሆን የምህረት ቃል ነበር። ወንድሞቹም ይበቀለናል ብለው በሰጉ ጊዜ እንዲህ አላቸው፡ “እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው።” (ዘጸ. 50፡ 20) እግዚአብሔር ከርሱ ጋር ያለ ሰው ልበ-ቅን ነው። በዮሴፍም ሕይወት የምናየው ይህንኑ ነው።

እግዚአብሔር በምርኮ ምድር ዮሴፍን በልጆች በባረከው ጊዜ ዮሴፍ ልጆቹን እያየ እግዚአብሔርን አመሰገነ። የመጀመሪያውን ልጅ “እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ የአባቴንም ቤት አስረሳኝ” ሲል “ምናሴ” ብሎ ሰየመው። ሁለተኛውን ደግሞ “እግዚአብሔር በመከራዬ አገር አፈራኝ” ሲል “ኤፍሬም” አለው። ዮሴፍ የተደረገለት በጎነት ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደሆነ አምኖ ለእርሱ እውቅናን ሰጠ። እግዚአብሔር መከራን ያሳልፋል። ዮሴፍ በአባቱ ቤት፤ በግብጽም ብዙ መከራ አይቷል። እግዚአብሔር ግን ያንን ሁሉ አስረስቶ በምስጋና አቆመው። ይህም ብቻ ሳይሆን ደግሞ በስደት ምድር አፈራው። ስኬታማና ባለ ሞገስ አደረገው። የንጉስ ባለሟልና እንቆቅልሽ ፈቺ አደረገው። የጣሉትን ወንድሞቹን ተቀባይና ታዳጊ አደረገው። እንደ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ በመከራው ሌሎችን (ያውም ጠላት የሆኑበትን ወንድሞቹን) አዳነ።

ወገኖቼ፦ እኛንም በእንግድነታችን ምድር የባረከን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። በእውነት አምላካችን ከኛ ጋር ሆኖ እየረዳን እዚህ አድርሶናል። ባለፍንበት ጎዳና ሁሉ በንስር ክንፍ የተሸከመን እግዚአብሔር ይመስገን። አሁንም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብናልፍ እንኳ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በመንገዳችን ሁሉ ከኛ ጋር እንዳለ ልብ እንበል። እርሱ መከራን ያስረሳል። ደግሞም በባእድ ምድር ፍሬያማ ያደርጋል። ምናሴና ኤፍሬም ያደረገልን እግዚአብሔር ይመስገን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page