top of page

ስምህ ማነው? (ክፍል ሁለት)

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለፈው ሳምንት የአብርሐምንና የሣራን እንዲሁም የያዕቆብን

ስሞቻቸውን እግዚአብሔር እንደለወጠላቸውና ይህንንም ያደረገው በምክንያት እንደሆነ

ተመልክተን ነበር። ዛሬ ደግሞ ከአዲስ ኪዳን ሁለት ስሞቻቸው የተቀየረላቸውን ሰዎች

እንመለከታለን። የመጀመሪያው ስሙ የተቀየረለት የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሐዋርያው ጴጥሮስ

ነው። በዮሐንስ ወንጌል 1:43 ላይ ኢየሱስ ሲናገር “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ

ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው አለ።” ወንድሙ እንድርያስ መሢሁን አግኝተናል

ብሎ ወደ ኢየሱስ እንዳመጣው ነው ወዲያው ኢየሱስ ስሙን የቀየረለት። ለምን ስሙን ቀየረው

ብለን ብንጠይቅ መልሱን የምናገኘው የጴጥሮስን ሕይወት ታሪክ ከቃሉ ስናነብ ነው።

ጴጥሮስ በባህርይው ፈጣንና ቀደም ቀደም ብሎ የሚናገር (Extrovert) ባህርይ ያለው

ሰው ነው። ነገር ግን እንደሰው የማያይና የማይፈርድ አምላክ ወደፊት በርሱ ሊሠራ ያሰበውን

የራሱን ዓላማ የሚፈጽም መሆኑን ለማመልከት ስሙን እንደቀየረለት እንረዳለን። ለምሳሌ

በማቴዎስ 16:18 ላይ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን ለጠየቃቸው ጥያቄ አስደናቂ መልስ ሲመልስለት

“አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ” አለ። አንዳንዶች ዐለት ያለው

ቃልና የጴጥሮስም ስም ዐለት ማለት ስለሆነ በጴጥሮስ ላይ ቤተክርስቲያን እንደተገነባች አድርገው

ያስተምራሉ። ነገረ ግን ይህ ክፍል የሚያሳየን ጴጥሮስ በመሰከረው እውነት ላይ ጌታ ቤተ

ክርስቲያኑን እንደሚመሠርት ነው። የጴጥሮስን ህይወትና አገልግሎት ስንመለከት ምንም እንኳን

ቢንገዳገድም እግዚኣብሔር እንደተናገረው በእምነቱ ፀንቶ በመቆም፤ ብዙዎችን ወደ መንግስቱ

በማምጣት መልካም ምስክር እንደሆነና ሰማዕት ሆኖ እንዳለፈ እናውቃለን።

ይህ ለኛም ትልቅ ፋይዳ አለው። በክርስቶስ ያመንን ሁላችንም አዲስ ስም አግኝተናል

ይህም ስም ክርስቲያን የሚል ነው። ይህም ክርስቶስ የእግዚኣብሔር ልጅ እንደሆነ የሚያምን፤

የክርስቶስን ፈለግ ዕለት ዕለት የሚከተልና ስላዳነው ጌታ ኢየሱስ አዳኝነት ለሌሎች ከመናገር

ወደኋላ የማይል መሆኑን የሚገልጽ ትርጉም የተሽከመ ስም ነው። ይህንን ስም እየኖርንበት ነው

ወይ? እንደስማችን እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን የዓለም ብርሃንና የምድር ጨው በመሆን

እንድናሳይ ጌታ ይርዳን።

ሁለተኛው ሰሙ የተቀየረለት ሰው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። በደማስቆ መንገድ ላይ

ጌታ ሲገናኘው የጠራው ሳውል ብሎት ነው (ሐዋ. 9)። ኣንዳንዶች የሳውልን ስም ኢየሱስ

የቀየረለት ይመስላቸዋል ግን አይደለም። ሳውል የዕብራይስጥ ስም ሲሆን ጳውሎስ ደግሞ የግሪክ

ስም ነው። ትርጉሙም ሳውል ማለት “የተለመነለት” ወይም “የተፀለየለት” “Asked for” or

“Prayed for” ማለት ሲሆን ጳውሎስ ማለት ደግሞ ትንሽ ወይም ጥቂት “little” or “small” ማለት

ነው። በጣም በርካታ ሰዎች ሳውል በመባል ይጠሩ ነበር ምክንያቱም የእሥራኤል የመጀመሪያው

ንጉሥ ስም ስለሆነ። ነገር ግን ከሳውል ይልቅ ለምን ጳውሎስ መባልን መረጠ ብለን ብንጠይቅ

ሐዋርያው ጳውሎስ በብዙ ቦታዎች ወንጌልን ለማድረስ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ (1ቆሮ

9:23) እንደሚለውና እራሱን የአህዛብ ሐዋርያ እንደሆነ እንደሚጠራው ሁሉ (ሮሜ 11:13) ነገስታት

በተጠሩበት ስም ከመጠራት ይልቅ ወንጌልን ለሌሎች ለማድረስ ያመቸው ዘንድ በህዝቡ ዘንድ

በተለመደው ስም እንደተጠቀመ ማየት እንችላለን። እንግዲህ እኔና እናንተም የራሳችንን፤

የወገናችንንና የአገራችንን ስም ለማስጠራትና ክብር ከመፈለግ ይልቅ በትህትና እራሳችንን

በማዋረድ ወንጌልን ለማድረስና የክርስቶስን ስም ለማስጠራት እንትጋ።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page