top of page

ሃሌ ሉያ።

መዝሙር 107 የምስጋና መዝሙር ነው። ዘማሪው እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን እየቆጠረ እዝቡ አምላካቸውን እንዲያመሰግኑ ይጋብዛል። መዝሙሩ የሚጀምረው “ሃሌ ሉያ” በሚል የሃሴት ምስጋና ነው። “ሃሌ ሉያ” የሚለው ቃል “ሃሌል” እና “ያህ” የሚሉ የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን የመጀመሪያው ቃል በደስታ፣ የለገደብ፣ በሙሉ ኃይል ማመስገን የሚለውን ሃሳብ ይይዛል። ሁለተኛው ቃል “ያህ” ደግሞ “ያህዌ” የሚለውን የእግዚአብሔርን ስም የሚወክል ነው። እንግዲህ “ሃሌ ሉያ” ስንል እግዚብሔርን በደስታ፣ በሙሉ ኃይልና መለቀቅ አመስግኑ የሚል የአምልኮና የምስጋና ጥሪ የሚያስተላልፍ ቃል ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳችን እግዚአብሔርን በዚህ መልኩ እንድናመሰግን በብዙ ስፍራዎች ተጽፎልን እናገኛለን። በተለይም ደግሞ ቃሉን በምስጋና በተሞሉት በመዝሙርና በራዕይ መጻሕፍት በ32 ቁጥሮች ውስጥ እናገኘዋለን። ከእነዚህም መካከል መዝሙር107 አንዱ ሲሆን፤ ሲጀምር “ሃሌ ሉያ” ይላል። መዝሙሩ እግዚአብሔርን በደስታና በግለት በዝማሬ አመስግኑ በማለት ጥሪ ሲያቀርብ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን በማሳሰብ ነው። እኛም ዛሬ እግዚአብሔር ያደረገልንን እያሰብን ሃሌ ሉያ ማለት ይገባናል።

በመጀመሪያ መዝሙረኛው እግዚአብሔር በደስታና በግለት አመስግኑ ብሎ የሚጋብዘን እግዚአብሔር ቸርና ምህረቱ ደግሞ ብዙ የሆነ አምላክ ስለሆነ ነው። የእግዚአብሔር ቸርነት በጎነቱን፣ ለጋስነቱን ሲያሳይ፤ ምህረቱ ደግሞ ይቅር ባይነቱንና በደልን አለመቁጠሩን የሚገልጽ ነው። እግዚአብሔር በዘመናት መካከል ለእስራኤል ቸርነት አድርጓል። በተለይም በዚህ መዝሙር ውስጥ ዘማሪው እንደሚዘረዝረው የእግዚአብሔር ቸርነት እስራኤልን ከጠላቶቹ በማዳን፣ ከተበተኑበት በመሰብሰብ፣ ምሪትን በመስጠት፣ ነፍሳቸውን ከበረከቱ በማጥገብ፣ እስራታቸውን በመስበር፣ የእጃቸውን ስራ በመባረክ፣ ተፈጥሮን በማዘዝና በሌሎችም ብዙ መንገዶች ተገልጿል። ምህረቱ ደግሞ እስራኤል ከአምላካቸው ዞር ባሉ ጊዜና በመከራ ሆነው ሲጮሁ ሰምቶ ከጥፋታቸው በመመለስ፣ ሞገሱንም በላቸው በማብዛት ተገልጿል።

ወገኖቼ፦ እኛም “ሃሌ ሉያ” እያልን እግዚአብሔርን በታላቅ ደስታና በግለት ማመስገን ይገባናል። በተለይም በዚህ በምንኖርበት አገር “የምስጋና ቀን” ሲከበር እኛ በተለየ መንፈስ በሕይወታችን የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ቸርነትና ምህረት እያሰብን ገደብ በሌለው ምስጋና በአምላካችን ፊት መቅረብ አለብን። እግዚአብሔር ቸርነቱን በሕይወታችን አብዝቷል። ለነፍሳችን የተጠመደውን የዲያቢሎስን ወጥመድ ሰብሮ ነጻ አውጥቶናል። ጨለማችንን ገፎ ወደ ራሱ ብርሃን አምጥቶናል። ሙታን ለነበርነው ሕይወትን ሰጥቶናል። በክፉው ፈቃድ ስንመላለስ የነበርነውን ልጆቹ አድርጎናል። የእጆቻችን ስራ ባርኮልን ምጋቦቱን አትረፍርፎልናል። ደግሞም ምህረቱ ገኖልን የፍርዳችንን የሞት እዳ በልጁ ላይ አድርጎ በሕይወት ኑሩ ብሎናል። እለት እለትም ምህረቱን በላችን አብዝቶ በፊቱ የምንቀርብበትን ጸጋ አብዝቶልናል። ሃሌ ሉያ።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page