top of page

አስቀድማችሁ...

“ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴ. 6:33)

በምድር ስንኖር የማንለውጣቸው አብረውን የተወለዱ የስብእና መገለጫዎች እንዳሉን ሁሉ በብዙ ጉዳዮች ደግሞ ምርጫ ማድረግን እንችል ዘንድ ነጻ ፈቃድ ተሰጥቶን የተፈጠርን ነን። ስለዚህም ባብዛኛው መልኩ ሕይወታችን የምርጫዎቻችን ውጤት ነው ለማለት እንችላለን። ለንፍሳችን ደህንነት የተዘጋጀውን መለኮታዊ መንገድ ከመከተል ጀምሮ፣ የትዳር ተጓዳኞቻችን፣ የተማርነውን ትምህርትና የምሰራውን ስራ እንመርጣለን። እያንዳንዱ ምርጫ ደግሞ የእድል ዋጋ ያስከፍላል። በጊዜአችን አንድ ነገር ስናደርግ በዚያው ጊዜ ሌላ ነገር የማድረግን እድል እናጣለን። አንድ ስፍራ ለመሄድ ስንወስን ሌላ ስፍራ ለመሄድ የምችልበትን እድል ሰውተን ነው። ስለዚህም ሁልጊዜ ሰው በተፈጥሮ ዝንባሌው የበለጠ አዋጭ የሚለውን የሚመርጥ አምክንዋዊ (rational)ነው ተብሎ የታሰባል። ነገር ግን ለሰው የተሻለ ምርጫ ምንድን ነው? በምርጫ ቅደም ተከተላችን መጀምሪያ መሰለፍ የሚገባው ማን ነው ወይንም ምንድን ነው? ለአንዳንድ ሰው ቤተሰብ የመጀመሪያ ነው። ለአንዳንድ ሰው ደግሞ ሞያ የመጀምሪያ ነው። ለሌሎች ደግሞ ሃብትን፣ ዝናን ወይንም ክብርን መፍለግ የመጀመሪያ ሊሆን ይችላል።

የእግዚአብሔር ቃል ግን ከማንኛው ነገር በፊት ማስቀደም ያለበን ነገር የግዚአብሔርን መንግስትና ጽድቅ መሆን እንዳለበት ይመክረናል። ቃሉ “... አስቀድማችሁ.የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ...” ይላል። ሰው ከሁሉ ነገር በፊት በሕይወቱ ቀዳሚ ማድረግ ያለበት እግዚአብሔርን ነው። ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሔር ክብር ነውና በሰው ሕይወት እግዚአብሔር ፊተኛውንና ዋናውን ስፍራ ሊይዝ ይገባዋል። ለእግዚአብሔር የምሰጠው የህይወታችንን እንጥፍጣፊ ሳይሆን ዋናውን “ስቡን” መሆን አለበት። ያስቀደምነው ነገር ይመራናል፤ ያስቀደምነው ነገር የምርጫዎቻችንን ቅደም-ተከተል ይወስናል። ያስቀደምነው ነገር አመለካከታችንን ይቀርጻል። ለአንድ አማኝ አንደኛ መሆን ያለበት ቤተሰቡ፣ ስራው፣ ሞያው፣ ንግዱ ወዘተ... ሳይሆን እግዚአብሔር መሆን አለበት። እግዚአብሔር በምንም ነገር ሁለተኛ ሆኖ አያውቅም። በመኖር እርሱ የመጀመሪያ ነው። ሰማይና ምድር ሳይፈጠሩ በመጀመሪያ እርሱ ነበር። እኛ ስንታሰብ እርሱ ነበር። በኃይልም በጥበብም በእውቀትም እርሱ የመጀመሪያ ነው። ማስተዋሉ አይመረመርም። እርሱን መጀመሪያ ካደረግን የሕይወት ቅደም ተከተላችን የተስተካከለ ይሆናል። ይህ ካልሆነ ግን ከፍቃዱ እውቀትና አደራረግ እንጎድላለን።

በእያንዳንዱ አካሄዳችን ላይ እግዚአብሔር ቀድሟል ወይ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። የቀደሙን የእምነት አባቶች አካሄዳቸው እግዚአብሔርን ያስቀደመ ነበር። እግዚአብሔርን ኋላ አድርገው ሕይወታቸውን ከማሰንበት ይልቅ እርሱን አስቀድመው በአንበሶች ጉድጓድ መጣል፤ በሚነድ እቶን ውስጥ መግባትን መረጡ። እግዚአብሔርን ተከታይ አድርገው ከመንገስ ይልቅ እርሱን አስቀድመው መከራ መቀበልን መረጡ። እርሱን አስቀድመው ድምጹን ሰምተው ወጡ። እርሱን ፊተኛ አድርገው ሕይወታቸውን አፈሰሱ። ነገር ግን ያስቀደሙት ጌታ፤ ዝርግፍ ጌጥ አድርገው የተዋቡበት ጌታ መታመኛና መምለጫ ሆናቸው። ምድር ባልተገባቻቸው ጊዜ እንኳ በደስታ ተሰናበቷት። በስጋም በነፍስም ላይ ስልጣን ያለውን ስላስቀደሙ ለስጋቸው አልሳሱም። ዘመናቸውን ሰጡት። በሰጣቸው ሁሉ አገለግሉት። አልተጣሉም። ዘራቸውም እንጀራን አልለመነም። ከክብር አልጎደሉም። ቀናቸውም በተፈጸመ ጊዜ በክብር ፊቱን ለማየት እየናፈቁ ሄዱ። በሕይወታችን ያስቀደምነው ማን ነው? ምንድነው?


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page