አብርሃም የእምነት ሰው
አብርሃም በኖረበት ዘመን እንደ ማንኛውም ሰው በዑር ከለዳውያን አገር የሚኖርና እንደ አባቱም ጣዖትን የሚያመልክ ሰው ነበረ (ኢያሱ 24፡2)። በዚያን ዘመን አንድን አምላክ ሳይሆን ብዙ ጣዖታትን ከሚያመልኩት ሰዎች ጋር አብሮ እያለ የእግዚአብሔር ጥሪ ወደ አብርሃም መጣ። “እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ ታላቅ ህዝብም አደርግሃለሁ፤ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፤ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ። አብርሃምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ።” (ዘፍ 12፡1-3)
ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ሶስት መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ማየት እንችላለን። የመጀመሪያው፡- አብርሃም በእግዚአብሔር ለመመረጥ ያደረገው ምንም ነገር አልነበረም። ከማንኛውም ሰው የተሻለ መልካም ሥራ ያልነበረውም፤ በጣዖት አምልኮ የታሠረ፤ በጨለማው ገዥ በዲያቢሎስ ቁጥጥር ሥር የሚኖር ተስፋ ያልነበረው ምስኪን ሰው ነበረ። ነገር ግን በምህረቱ ባለጠጋ የሆነው እግዚአብሔር አብርሃምን የመረጠው በዘላለም ፍቅሩ ስለ ወደደው ብቻ ነው።
እኔና እናንተም በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን የነበርን፤ በዚህ ዓለም ገዥ እንዲሆን ጌታ ስልጣን በሰጠው በዲያቢሎስ ቁጥጥር ሥር የነበርን፤ ወደ ሞት የምንነዳ ተስፋ ያልነበረን ሰዎች ነበርን። ነገር ግን ሃሌሉያ! እግዚአብሔር በምህረቱ ባለ ጠጋ ስለሆነ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሰጠን። (ኤፌ 2፡1-5)። የኔ አባት ልጅ እያለ ከአያቴና ከመላው ቤተሰብ ጋር በመሆን ጣዖትን ያመልኩና ለዲያቢሎስ መስዋዕት በማቅረብ በጨለማ ይመላለሱ ነበር። ለሰይጣን የሚቀርበውን መስዋዕት በትክክል አላቀረባችሁም በማለት ሴት አያቴን ገድሎ አባቴንና መላውን የቤተሰብ አባላት አንድ በአንድ እገላችኋለሁ ብሎ በመዛት ላይ እያለ ነበር ከአሜሪካና ካናዳ ወደ ኢትዮጽያ በሄዱት ሚስዮናውያን አማካይነት ወንጌልን ሰምተው በኢየሱስ በማመን ከጨካኙ ዲያቢሎስ እጅ አምልጠው ነጻ በመውጣት የወንጌል አገልጋዮች የሆኑት። ምናልባት ዛሬም ጠላት ዲያቢሉስ ሞትን እያወጀባችሁ በፍርሃት የምትመላለሱ ሰዎች ካላችሁ የምሥራች ልንገራችሁ እግዚአብሔር ይወዳችኋል። እግዚአብሔር እኛ ሳንወደውና ሳናውቀው በኃጢአታችን ስንበድለውና ስናሳዝነው እያለን አንዲያ ልጁን ኢየሱስን ስለ እኛ በመስቀል እንዲሞት አሳልፎ በመስጠት ፍቅሩን በተግባር አሳየን። ስለዚህ ኢየሱስን በማምን ብቻ ከዘላለም ሞት ፍርሃት ነጻ በመውጣት በሰላምና በደስታ ለመኖር ትችላላችሁ።
ሁለተኛው፦ እግዚአብሔር አብርሃምን የጠራው ለበረከትና ለትልቅ የከበረ ዓላማ ነበረ። ከጥሪው ጋር አንድ ላይ እግዚአብሔር በራሱ አነሳሽነት ታላቅ ህዝብ አደርግሃለሁ፤ እባርክሃለሁ፤ አከብርሃለሁ፤ የምድር ወገኖች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ...እያለ ለአብርሃም ቃል ኪዳን ሲገባለት እናያለን። ይህ የሚያሳየን የእግዚአብሔር ጥሪ ለማይረባ፤ ለጊዜያዊና ለምድራዊ ነገር እንዳልሆነ ነው። አንድም ልጅ የሌለውን አብርሃምን ታላቅ ህዝብ ለማድረግና የምድር ወገኖችን ሁሉ በርሱ ለመባረክ ቃል ሲገባለት እናያለን። ወገኖቼ ዛሬም እግዚአብሔር የጠራን ለጊዜያዊው የምድር ኑሮ ተድላና ምቾት ሳይሆን ዘላለማዊ የሆነውና የከበረው የእርሱ አጀንዳ በኛ እንዲፈጸም ሊጠቀምብን ነው! ዛሬ ያለንበትን ትንሽ ሥፍራ ሳይሆን እግዚአብሔር ያየልንን ትልቅ ነገር በእምነት እያየን ልንጓዝ ይገባናል።
ሶስተኛው፦ አብርሃም እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል አመነ ታዘዘም። በዓይን የሚታይ ምንም ነገር በሌለበት እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል አብርሃም አመነ። አብርሃም ከእግዚአብሔር የተቀበለውና ያመነው የከበረውን የእግዚአብሔርን ቃል ነው። እግዚአብሔር ከተናገረ እንደሚያደርገው በማመን አብርሃም እግዚአብሔርን ታዘዘ። እምነትና መታዘዝ አብረው የሚሄዱ ናቸው። እኔና እናንተም ለእግዚአብሔር ቃል ዋጋ በመስጠት የቃሉን ኃይልና ክቡርነት በማመን እራሳችንን አሳልፈን ልንሰጥና ልንታዘዝ ይገባናል። በተለይም ባለንበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን እግዚአብሔርን ማመንና መታዘዝ በተለያየ አቃጣጫ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል። እንደ አብርሃም በፍቅሩ ለከበረና ትልቅ ዓላማ የጠራንን እግዚአብሔርን በማመንና በመታዘዝ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅተናል?