top of page

ሁሉን የሚያስጥል ፍቅር

“ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት።" ሉቃስ 5፡11

ታሪኩን ስንመለከት ስፍራው "ጌንሳሬጥ" የተባለ ሲሆን ኢየሱስ በባህሩ ዳር ቆሞ እጅግ ብዙ ህዝብ እያስተማረ እንደነበር፣ በባህሩ ዳር ግን በዓሣ ማጥመድ ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች፣ በዚያን እለት ግን ምንም እንኳን የአሣ ማጥመድ የረጅም ጊዜ ልምዱ ቢኖራቸውም ሌሊቱን ሙሉ ደክመው አንድም ዓሣ መያዝ ያልቻሉ፣ ከዚህም የተነሳ ተስፋ ቆርጠውና ባዶውን ታንኳቸውን ከዳር ላይ በማቆም መረባቸውን በማጠብ ላይ እንደነበሩ ይናገራል። ከድካማቸው የተነሳ ይመስላል በባህሩ ዳር የሚደረገውን ግርግር፣ የህዝቡን ግፊያና ህዝቡን የሚያስተምረውንም መምህር ከቁብ አልቆጠሩትም ነበር። ኢየሱስ ግን ከነዚህ ባዶ ታንኳዎች ወደ አንዲቱ ወደ ስምኦን (በኋላ ጴጥሮስ ወደተባለው) ወደ ሆነችው በመግባት ጥቂት ከምድር ራቅ እንዲሉ ጠየቀው። ባዶነት በኢየሱስ ሲሞላ፣ ማለትም ኢየሱስ ሲገባበትና ስፍራውን ሲቆጣጠረው፣ ተስፋ የቆረጠ የነበረ ህይወት ከአፉ በሚወጣው ቃል ዘወትር በበረከቱ እየታጨቀ፣ እየተሞላና እየበዛ ይኖራል። በታንኳችን ውስጥ ያለው ጌታ ማንነትና ፍቅር የመታወቁ መጠን እየጨመረ ሲመጣ ደግሞ ከእጁ የተቀበልነውን የሥጋ በረከቶች እንኳን ወዲያ በማሥቀመጥ ሁሉን ትቶ እርሱን ብቻ ለመከተል ያስወስናል።

ወደ ክፍሉ ስንመለስ ታድያ ጌታ ኢየሱስ ማስተማሩን ከጨረሰ በኋላ የተመለሰው ወደ እነ ስምኦን ችግር ነበር። "ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ..." በማለት ምሪትንና ቃልን ሰጠው። ጌታ ይህንን ሲናገር ታድያ እነ ስምኦን ዓሣን ለመያዝ ሌሊቱን ሙሉ እንደደከሙና ሲነጋም ተስፋን ቆርጠው ባዶ መረባቸውን እያጠቡ እንደነበር ያውቃል። ነገር ግን በዚህ ተስፋ በቆረጡበትና በባዶው ነገራቸው ላይ ቃልን ሲያወጣበት ስምኦን “...በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ አለው። ይህንንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ መረቦቻቸውም ተቀደዱ” በማለት ጌታ የተናገረውን ቃል በእምነት በመቀበልና እንደ ቃሉም በማድረግ የተትረፈረፈና የተጨቆነ በረከትን በቃሉ እንደተሞላ እናያለን። ይህ ያደረገው ተዓምራት ደግሞ አብሮት ያለው ጌታ በእርግጥ ጌታ እንደሆነ እንዲያውቅና በህይወቱ ታላቅ ውሳኔን እንዲያደርግ አድርጎታል።

ከውሳኔዎቹም የመጀመሪያው ኃጢያተኛ መሆኑን በመናዘዝ በእውነተኛ ንስሓ በጌታ ፊት ራሱን ማዋረድ ነበር። ስምኦን ጴጥሮስ አሁን ከእርሱ ጋር ያለው በእርግጥ ጌታ እንደሆነ በማወቅ እራሱን በጌታ ፊት በማዋረድ ፣ ኃጢያተኛ እንደሆነ ተናዘዘ። እንደውም ጌታ ከእርሱ ጋር ሊሆን እንደማይገባውና ከእርሱም እንዲለይ ለመነው። “ጌታ ሆይ እኔ ኃጢያተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው” ይላል። ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር በውስጣችንም ያለው የተቀበልነው ጌታ ማንነት በደንብ እየገባንና እያወቅነው ስንመጣ ነው እውነተኛ ማንነታችንን በፊቱ በማዋረድ፣ የተሰጠን ህይወት እንደኛ ማንነት ቢሆን የማይገባን እንደነበረና ጌታ ግን ከታላቅ ፍቅሩና ከምህረቱ የተነሳ ይህንን ህይወት እንደሰጠን በማወቅ በትህትና የምንገዛለት። ስምኦንም ወደዚች ባዶዋን ውኃው ዳር በሥሱ ማዕበል ትንገዋለል ወደነበረችውና ዓሣ ዓሣ ወደምትሸተው ታንኳው ውስጥ ገብቶ፣ ተስፋ ቆርጦና ደክሞ ከነበረው ሰው ጋር የተቀመጠው ጌታ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረና ሁሉም ደግሞ የሚታዘዙለት ጌታ መሆኑን ሲያውቅ በእውነተኛ ንስኃ በፊቱ ለመውደቅ ወሰነ። ይህን እውነተኛ ውሳኔ በስምኦን ጴጥሮስ ላይ የተመለከተው ጌታ ታዲያ ለታላቁ የእግዚአብሄር መንግስት ሥራ ስምኦንን “አትፍራ ከእንግዲህ ወዲያ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ...” በማለት ፍቅር በተሞላበት ቃና ሲጠራው እንመለከታለን። ይህ ደግሞ በእለታዊ ኑሮ ላይ የሚያስጨክን ትልቅ ውሳኔን የሚጠይቅ ጉዳይ ቢሆንም የጌታ ፍቅር የገባው ሰው ግን እንደታላቅ እድል በመቁጠር ሁሉንም ትቶ ለመከተል አይከብደውም።

ስለዚህ የስምኦን ቀጣይ ውሳኔ የነበረው ያለውን ሁሉ ጥሎ ጌታን መከተል ነበር። የጌታ ፍቅርና ታላቅነት ስለገባው ይህን ውሳኔ ለመወሰን ጊዜ ቀጠሮ አላስፈለገውም። ነገር ግን ሁሉንም፣ ማለትም ጌታ አትረፍርፎ የሰጠውን በረከት ጨምሮ ለዘመናት ይተዳደርባት የነበረችውን ታንኳውንም ሆነ መረቡን፣ የዓሣ ማጥመድ ሥራውን ሳይቀር ትቶ ጌታን ተከተለው። እንግዲህ ወገኖቼ ሰማይንና ምድርን፣ በውስጣቸው ያለውን ሁሉ የፈጠረ፣ ሁሉ በቃሉ የሚታዘዙለት አምላክ ወደ እኛ በሃጢያት ተለውሰንና ውስጣችን በባዶነት፣ ተስፋ በመቁረጥ ተሞልቶ ወደ ነበረው ህይወታችን ትሁት ሆኖ ያን ክብሩን ሁሉ ትቶ በመምጣት ህይወታችንን ቀይሮ፣ ሁለንተናችንን ተቆጣጥሮ፣ ባዶነታችንን በቃሉ እየሞላና በበረከቱ እያትረፈረፈ የሚያኖረን ጌታ ፍቅሩን ምን ያህል ተረድተነው ይሆን! ከዚህም በላይ የመንግስቱ አገልይ ካህናቶቹ ያደረገን የማያልፍንም የዘላለም እርስት ያዘጋጀልን ጌታ የፍቅሩን መጠን ታላቅነት ያሳየናል። ታድያ ይህ ፍቅሩ በእውነት ሲገባን ልክ እንደ ጴጥሮስ ራሳችንን በእውነተኛ ንሰሃ በጌታ ፊት በማዋረድና ያለንንም ሁሉ በፊቱ በመጣል ሁሉንም ትተን እንከተለዋለን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page