top of page

እምነታችሁ የት ነው?

“.......ወደ ባህር ማዶ እንሻገር አላቸው ....... አውሎ ነፋስም በባህር ላይ ወረደ ፣ ውኃም ታንኳይቱን ይሞላ ነበርና ይጨነቁ ነበር። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውኃውን ማዕበል ገሰጻቸው ተውም፣ ጸጥታም ሆነ። እርሱም

'እምነታችሁ የት ነው? አላቸው። ......” ሉቃስ 8፡ 22-25 ይህ ጥያቄ የቀረበው የነበራቸውን ነገር ሁሉ በመተው ኢየሱስ ክርስቶስን የተከተሉ፣ በየስፍራው

ያደረጋቸውን ድንቅና ታምራቶች የተመለከቱ፣ ጌታም ለአገልግሎቱ የለያቸውና በሓዋሪያነት የሾማቸው ደቀመዛሙርቱ ነበር። ጌታም ደቀመዛሙርቱን ለአገልግሎት ከሚያዘጋጅበት መንገዶች አንዱ እምነትን ማለማመድ ነበር። ምክንያቱም እምነት ለመንፈሳዊ ህይወትም ሆነ ለአገልግሎት ዋነኛና የመጀመሪያው ቁልፍ ነውና። ታዲያ እምነትን የሚያለማምዳቸው በቃል ስለእምነት ከማስተማር ባሻገር በሚያደርጋቸው ታምራትና ድንቆችም በተግባር በማሳየት፣ እንዲሁም የነሱንም እምነት በመፈትን ነበር። ስለዚህም ከላይ በተጠቀሰው ክፍል ውስጥ የምንመለከተው የደቀመዛሙርቱ እምነት ተፈትኖ ሲወድቅና ከወዴት እንደጣሉት ሲጠየቁ ነው። እንግዲህ እምነት የምንጥለውና የምናነሳው ሲሆን ስንጥለውም ሆነ ስናነሳው በህይወታችን የሚከሰቱ ነገሮች እንዳሉ ከክፍሉ የምንማረው ነገር አለ።

እምነት ስንል ታዲያ በተፈጥሮ በምናያቸው ነገሮች ላይ የተመሰረተውን እምነት፣ ለምሳሌ- ሰኞ ላይ ሆነን ማክሰኞ እንደሚመጣ፣ የቆምንበት መሬት ችሎ እንደሚሸከመን፣ ወይንም የተቀመጥንበት ወንበር እንደማይጥለን የምናምነው አይነት እምነት ሳይሆን፣ በማይታየውና መነሻው ከእግዚአብሄር አፍ በሚወጣው ቃል ላይ የተመሰረተውን እምነት ማለታችን ነው። ምክንያቱም መጽሓፍ “እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሄር ቃል ነው” ሮሜ 10፤17 በማለት በእግዚአብሄር ላይ የምንታመንበት እምነትና መገኛውም የእግዚአብሄርን ቃል በመስማት ብቻ እንደሆነ ይነግረናል።

በጠቀስነው ክፍል ጌታ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ከገባ በኋላ “ወደ ባህር ማዶ እንሻገር” የሚልን ቃል ሲነግራቸው እንመለከታለን። እርሱ የሚያምነው “እንሻገር” ይሚለውን ቃሉን ስለሆነ በመንገድ ላይ ሊገጥማቸው ስለሚችለው ችግርና ስለጥፋት ከቶ አያሳስበውም። ስለዚም እንደሚሻገሩ አምኖ በታንኳው ውስጥ ተደላድሎ ተኝቶአል። ወደመሃል ሲደርሱ ግን እምነታቸውን የሚፈትን ታላቅ ነፋስና ማዕበል ተነሳ፤ ይህም ማዕበልና ነፋስ ከግዙፍነቱም የተነሳ ለኃዋሪያቱ ሞትንና ጥፋትን ይሰባክቸው ጀመር። የድምጹም ብዛት “እንሻገር” የሚለውን የኢየሱስን ቃልና አብሮአቸው ያለውን ብዙ ትላላቅ ታምራቶችን በፊታቸው ያደረገውን ኢየሱስን አስረሳቸው። ስለዚህም ከመሻገር ይልቅ ጥፋትና ሞት ታያቸው። “እንሻገር” በሚለው ቃሉ ላይ የተመሰረተውን ይዘውት የተነሱትን እምነታቸውን ነፋሱና ማዕበሉ አስጣላቸው። ከዚህ የተናሳ በውስጣቸው ፍርሃትና ተስፋ መቁረጥ በመፈጠሩ ጸሎታቸው “ወየው ጠፋን፣ ስንጠፋ አይገድህም ወይ!!” የሚል ሆነ። ጌታ ግን አስቀድሞ ማዕበሉንና ነፋሱን ከገሰጸው በኋላ በመቀጠል የገሰጸው ደግሞ ደቀመዛሙርቱን “እምነታችሁ የት ነው?” በማለት ነበር። ምክንያቱም ይህ ነፋሱንና ማዕበሉን የመገሰጽና የማቆም ስራ የጌታ ሳይሆን የነርሱ ነበርና። ጌታ ኢየሱስ የፈለገው እርሱን በፍርሃት ተሞልተው ከመቀስቀስ ይልቅ የተነሳውን ወጀብ በእጃቸው ያለውንና በመጀመሪያ ሲነሱ ይዘውት የነበሩትን እምነታቸውን ተጠቅመው ራሳቸው ጸጥ እንዲያደርጉት፣ እምነታቸውንም ሲለማመዱት ማየት ነበር። ነገር ግን ከዚያ ይልቅ በተነሳው ወጀብ እምነታቸውን ሲጥሉና ፈተናውን ሲወድቁ እንመለከታለን። ጌታም የጣሉትንም እምነት እንደገና ከጣሉበት ፈልገው እንዲያነሱት አስገነዘባቸው።

እንግዲህ ወገኖቼ እኛም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቶች እንደመሆናችን ሁል ጊዜ በቃሉ ላይ በተመሰረተው እምነታችን ልንመላለስ ይገባናል። ክርስትና ደግሞ ከእምነት የጀመረ የመውጣት ጉዞ ነው። ይህ ጉዞ ደግሞ ተሻግረን የምንደርስበት መድረሻ ያለው የክብር ተስፋ የሚወረስበት ጉዞ ነው። ይህን ጉዞ ስንጓዝ ታዲያ አልጋ በአልጋ በሆነ ጎዳና ሳይሆን በመንገድ ላይ የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎ ሊገጥሙን ይችላሉ፤ የዚህን ጊዜ ታዲያ “ተሻገሩ” ባለን ጌታና በነገረን ቃል ላይ ያለንን፣ በጉዞው መጀመሪያ ላይ ይዘነው የወጣነውን የእምነት በትራችንን መዥረጥ በማድረግ “አትሻገሩም፣ ትሞታላችሁ” እያለ መማጓራት በሚሰብከን ማዕበል ልይ በመዘርጋት እምነታችንን ስንጠቀምበት ማየት ጌታችንን ከምንም በላይ ያስደስተዋል። እምነትን መጣል ግን በእኛ ላይ ፍርሃትንና ጭንቀትን፣ ተስፋ መቁረጥን ከማስከተሉም በላይ ጌታንም ያሳዝነዋል። ስለዚህ እምነታችንን በማዕበሉ ላይ የምናነሳ እንጂ ማዕበሉ እምነታችንን የሚያስጥለን ልንሆን አይገባንም። እምነታቸውን ከሚያነሱ ጋር ጌታም ይነሳልና እምነታችሁን አንሱ።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page