በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ።
“በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።” (2 ዜና 7:14)
ክርስቲያኖች ካሉን ተስፋዎች መካከል በከፍተኛ ስፍራ የምናስቀምጠው አንዱ አምላካችን እግዚአብሔር ጸሎትን ሰምቶ የሚመልስ መሆኑ ነው። በዚህ ስፍራ እንደምናነበው እግዚአብሔር በስሙ ለተጠሩት ሕዝቡ የገባው ተስፋ አለ። ተስፋው ግን ቅድመ ሁኔታዎች አሉት። የመጀመሪያው በእግዚአብሔር ፊት ትሁት መሆን ነው። ሁለተኛው የእግዚአብሔር ፊት በጸሎት መፈለግ ነው። ሶስተኛው ከክፉ መንገድ መመለስ ነው። ይህ ሲሆን እግዚአብሔር ይሰማናል፣ ይቅር ይለናል፣ ደግሞም ይፈውሰናል።
ለሚገጥሙን ማንኛውም ግላዊና አገራዊ ጉዳዮች ትልቁ መፍትሔ በእግዚአብሔር ፊት በትህትና መጸለይ ነው። በአውዱ ላይ እደምንመለከተው ይህ ትልቅ የጸሎት መልስ ተስፋ የተሰጠው አገራዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ነው። እግዚአብሔር ህዝቡን ለመቅጣት ዝናብን ቢከለክል፣ ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ቢያዝ ወይንም ቸነፈርን ቢያዝዝ ለዚህ አገራዊ ችግር መፍትሔ ያለው በስሙ በተጠሩት ህዝቡ ዘንድ ነው። አሳሳቢ ሁኔታዎች ሲገጥሙ በትህትና በታላቁ ጌታ ፊት በጸሎት መውደቅ ወሳኝ ነው። በተለይም ቤተ ክርስቲያን ዋናው ማድረግ ያለባት ይህ መሆን አለበት። የራሳችንን ማስተዋል ተጠቅመን ችግሩን ለመፍታት ከመጣር ይልቅ አስቀድመን እግዚአብሔር ሆይ አባክህን ይህንን ጉዳይ ተመልከተው ብለን በጸሎት ብንቀርብ መልስ ከሰማይ ይመጣልናል።
የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ ወደ እርሱ በምልጃ መሮጥ ነው። እርሱን የሙጥኝ ማለት ነው። ሰው በመከራው ጊዜ የበለጠ የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ አለበት። የአገር ሸክም የከበዳቸው አባቶች ያደርጉ የነበረው የሕዛባቸውን መተላለፍ ይዘው ፊቱን መፈለግ ነው። ነህምያ የኢየሩሳሌምን መፍረስና መቃጠል ሲሰማ ለአያሌ ቀናት በጾምና በጸሎት በንስሃም የእግዚአብሔርን ፊት ፈለገ። በእግዚብሔር ፊት እንደ መሪ የሕቡን መተላለፍ ይዞ ቀረበ። አለቀሰ። ነስሃ ገባ። ነህምያ መፍትሔ ፍለጋ ያገለግለው ወደ ነበረው ንጉስ አልገባም። ወይንም አስቀድሞ ችግሩን ለመፍታት አልተንቀሳቀሰም። ነገር ግን አስቀድም የአምላኩን ፊት በጽኑ ፈለገ። ቃል-ኪዳኑን አስታወሰ። ምሕረትና ሞገስን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ዘምበል አለለት። ዳንኤልም የኢየሩሳሌም የሰባ አመት ምርኮ የሚፈጸምበትን ከመጽሐፍ ሲረዳ ያደረገው አንድ ነገር በንስሃ የአምላኩን ፊት መፈለግ ነበር። እግዝዚአብሔርም በፊቱ የጸለዩትን የንስሃ ጸሎት ሰምቶ አሰባቸው። ከውድቀትም አዳናቸው።
ወገኖቼ፦ ለችግራችን መፍተሔ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው። አይኖቻችንን ወደ ተራሮች ብናነሳ እርዳታ አናገኝም። እርዳታችን ያለው ከሰማይ አምላክ ዘንድ ነው። ለምንኖርባት ከተማ ችግርም ሆነ ለተወለድንባት አገር ችግር እግዚአብሔር ምህርትን የሚያደርገው በሰሙ የተጠራነው ህዝቡ እራሳችንን አዋርደን እንደ ነህምያ በጸሎትና በንስሃ በፊቱ ስንቀርብ ነው። ያን ጊዜ የሰማይ አምላክ ይሰማናል። ይቅር የለናል። ስብራታችንንም ይጠግናል። አሜን!