top of page

የሕይወት ውኃ

ጌታ በምድር በነበረበት ጊዜ አይሁድ ከሳምራዊያን ጋር ስለማይተባበርሩ ምንም እንኳ ከይሁዳ ወደ ገሊላ ለመሄድ አቋራጭ የንነበረው መንገድ በሰማሪያ በኩል ቢሆንም አይሁዳዊያን ግን አቋራጩን መንገድ አይመርጡም ነበር። በዮሐንስ 4 ላይ እንደምንመለከተው ግን ጌታ ኢየሱስ በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆኖበት ነበር። ምን ግድ አለው ብለን ብንጠይቅ ግድ ያለው ነገር ቢኖር መደረስ ያለባት ነፍስ ነበረች። ከክፍሉ እንደምንመለከተው ጌታ ኢየሱስ መንገድ ከመሄድ ደክም በሰማሪያ፣ ሲካር ከተማ በያቆብ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። ጊዜው ቀትር ላይ ነበር። በዚያኑ ሰአት ደግም ከሰማሪያ አንዲት ሴት ውሃ ልትቀዳ መጣች።

ይህቺ ሴት የተቸገረች ሴት ነች። በመጀመሪያ በምንም መልኩ በቀጥር ውሃ ለመቅዳት ወደ ጉድጓድ አይመጣም። ውሃ የሚቀዳው ወይ በጠዋት ነው አለያው ጥላ ሲበርድ ነው። በልማድ ቀትር ጋኔን የሚወጣበት ነው። ለዚህም ሳሆን አይቀርም ቃሉ እግዚአብሔር ከቀትር ጋኔን እንደሚጠብቀን የሚናገረው። (መዝ. 91፡6) ስለዚህም በቀትር ሰው ወደ ውሃ ጉድጓድ ዝር አይልም። ይህች ሴት ግን ውሃን በቀትር ትቀዳለች። ተሰውራ-- ሰው ሳያያት የምትወጣና ይምትገባ ትመስላለች። ስለዚህም ከማህበረሰብ የተገለለች ሴት እንደነበረች የክፍሉ አውድ ያሳያል። ይህቺ ሴት የተጠማች ሴት ነች። የተጠማችው ውሃ ሳይሆን ሕይወት የተጠማች ሴት ነበረች። ብዙ ባሎች በመቀያየር ጥማቷን ለማርካት ሞክራለች። አምስት ባሎች አግብታ የፈታች አሁን ባሏ ካልሆነ ስድስተኛ ወንድ ጋር የምትኖር ናት። የባሎች መቀያየር የነፍሷን ረሃብ አላጠገበም። ሴቲቱ በሳምራዊነቷም በሴትነቷም በይሁድ የተናቀችም ነበረች። ሴቲቱ የእምነትም ችግር ነበራት። ለእግዚአብሔር የት ወይንም እንዴት እንደሚሰገድ አታውቅም።

እንግዲህ ግታን በሰማሪያ እንዲያልፍ ግድ ያለው የዚህች ቆስቋላ ሴት የሕይወት ጥም ነበር። የውስጥ ጥማቷን የሚያውቅ ጌታ “ተጠማሁ” ብሎ ቀረባት። ሰው ቀርቧት የማይውቅ ይህች ሴት አይሁዳዊ ውሃ አጠጪኝ ቢላት ተገረመች። እንዴት ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከኔ ውሃ ትለምናለህ አለችው። በውስጣ ግን “ጉዴን ባያውቅ” ነው ማለቷም አይቀርም። ጌታ ግን እርሱን ብታውቅ ጥማትዋን ሁሉ የሚፈውስ የሕይወትን ውሃ እንደሚሰጣት ተናገራት። እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ለዘላለም አይጠማም አላት። ይልቁንም ከጌታ ውሃ የሚጠጣ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል አላት።

ወገኖቼ፦ ለነፍሳችን እርካታ የሚሰጠው ጌታ ብቻ ነው። ብዙ የውሃ አይነት ጠጥተን ለመርካት ሞክረን ይሆናል። በገንዘብ ውሃ ነብስ አትረካም፤ በእውቀት ውሃ ነፍስ አትጠግብም፤ በዝና ውሃ ጥሙ የተቆረጠ የለም፤ የስልጣንም ውሃ ነፍስን አያሳርፍም። ጌታችን ለዚች ለተጠማችና ለተቸገረች ነፍስ እንዳላት “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል” (ቁ.13)። ነፍስን የሚያረካም ነፍሳችን ፈጣሪዋንና ጌታዋን ስትገናኝ የምትጠጣው የሕይወት ውኃ ብቻ ነው። ያንጊዜ ጥማትን የሚቆርጥ ምንጭ ከውስጥ ይፈልቃል። ምንጩ በምፈልቅበት ጥማት የለም። ይህቺም ሴት የውስጧ ጥም ሲቆረጥ እንስራዋን ጥላ ይህንን የሕይወት ምንጭ ለሌሎች ለመናገር ሮጠች። ወገኖቼ፦ በውስጣችን የሕይወት ምንጭ አለ። ያሳረፈንና የሚያሳርፈን ይሄ የሕይወት ምንጭ ብቻ ነው። ክብር ለዘላለም ለጌታ ይሁን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page