መንፈስ ቅዱስ ወቃሽ (ገላጭ) መንፈስ።
“እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል።” (ዮሐ. 16:8) መንፈስ ቅዱስ አሁን ሶስት ወሳኝ ስራዎች ያደርጋል። አንደኛ ስለ ኃጢያት አለምን
ይወቅሳል። ሁለተኛ የክርስቶስን ጽድቅ ለአለም ይገልጻል። ሶስተኛ ስለ የመጨረሻውን ፍርድ ያስጠነቅቃል። በዚህ ክፍል እንደምናየው በኃጢያት እና በፍርድ መካከል የክርስቶስ ጽድቅ መካከለኛ ሆኖ አለ። ኃጢያት ወደ ፍርድ ይወስዳል ነገር ግን ከፍርድ መውጫው መንገድ የክርስቶስን ጽድቅ መቀበል ብቻ ነው።
መንፈስ ቅዱስ አለምን ስለ ኃጢያት ይወቅሳል። ይህም ሰው ኃጢያተኝንቱን አምኖ ክርስቶስን በመቀበል ይድን ዘንድ ነው። ወንጌል ሲሰበክ በክርስቶስ ኢየሱስ የማያምኑትን መንፈስ ቅዱስ ይወቅሳቸዋል። ይህ “ይወቅሳቸዋል” የሚለው ቃል መንፈስ ቅዱስ የሚሰራውን ኃጢያትን የመግለጥ ስራ የሚያሳይ ነው። ይህ የመግለጥ ስራ ደግሞ ሰው ወደ ራሱ ተመልክቶ በኃጢያቱ እንዲወቀስና ወደ ንስሃ ይመጣ ዘንድ ነው። ለዚህ ነው ሐዋሪያው ጴጥሮስ በበዓለ አምሳ ቀን ከተለያየ ቦታ መጥተው በኢየሩሳሌም ለተሰበሰቡት ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወንጌሉን በስልጣን ከሰበከ በኋላ የሰሙት ሰዎች ልባቸው ተነክቶ “ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁ (ሐዋ. 2:37)። በዚህን ጊዜ ሰዎቹ በኃጢያታቸው እንደተወቀሱ አስተውሎ ሐዋሪያው ጴጥሮስ “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” አላቸው (ቁ. 38) ይህንን ቃል ከሰሙት በዚያን ቀን ሶስት ሺህ ሰዎች እንደዳኑ እናነባለን (ቁ. 41)። ቃሉ ሲሰበክ ሰዎች ኃጢያተኝነታቸው ተሰምቶአቸው እንዲወቀሱ፣ ብሎም ንስሃ እንዲገቡ ያደረገው መንፈስ ቅዱስ ነው።
መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ጽድቅ ይገልጣል። አሁን ጌታችን በአካል በመካከላችን የለም ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ አለ። መንፈስ ቅዱስ ጌታን ያከብረዋል። በጌታም የመጣውን የመዳን ጽድቅ ለሰዎች ሁሉ ይገልጻል። ይህም መጽሐፍ “አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው” እንደሚል (ሮሜ 3፡ 21- 22) መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ያገኘነውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ ይገልጻል። እንዲሁም ደግሞ ለኛ ለምናምን የእግዚአብሔርን ጽድቅ እያበራ በጽድቅ እንድንመላለስ አቅም ይሰጠናል። ከጽድቅም ሃሳብ ስንስት ወቅሶ ይመልሰናል። አንዳድ ጊዜ ሰዎች ጌታን ከተቀበሉ በኋላ አንዳንድ አለማዊ ልማዶችን ይዘው ይቀጥላሉ። ጥቂት ቆይተው ግን እንዲህ አይነቱን ነገር ማንም ምንም ሳይላቸው ይተውቷል። ለዚህ ምክንያቱ መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስን ጽድቅ ስለሚያበራላቸው በቀደመው ሕይወት ለመቀጠል ስለማይችሉ ነው።
መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሊመጣ ያለውን በሰይጣን እና በተከታዮቹ የሚፈጸመውን የመጨረሻ ፍርድ ይገልጣል። ዳቢሎስ ተፈርዶበታል። በመጨረሻ የወንድሞች ከሳሽ ይጣላል። ጠላታችን የወደቀ፣ የተፈረደበት የፍርድን ፍጻሜ የሚጠብቅ እንደሆነ በመግለጥ በጥላታችን ፊት በኃይል እንድንገለጥ የሚያደረገን መንፈስ ቅዱስ ነው። ወገኖቼ፦ የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ እየሰማን እንመላለስ። እርሱ ከኛ ጋር ነው። ስለ ኃጢያት ይወቅሳል፤ የክርስቶስን ጽድቅ ይገልጻል እንዲሁም የመጨረሻውን ፍርድ ያሳውቃል። አሜን!