ጨለማችን በርቷል!
ሁላችንም እንደምናስተውለው በገና ወቅት ከቀናት በፊት በየቤቱና በየአካባቢው ልዩ ልዩ መብራቶች ይሰቀላሉ። መብራቶቹ ደማቅና በልዩ ልዩ ቀላማት ያሸበረቁ ሆነው ለምሽቱ ጨለማ የተለየ ውበት ያጎናጽፉታል። በእውቀትም ሆነ በልማድ መብራቶቹ የሚያስተላልፉት መልእክት አለ። መልእክቱ ብርሃን ወደ አለም መጥቷል የሚል ነው። ይህ ወደ እኛ ከላይ የመጣው ብርሃን ለተቀበሉት ሁሉ ሕይወት የሚሰጥ የሰዎችን ጨለማ የሚገፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ነብያትና ሐዋሪያት ስለዚህ አስደናቂ ብርሃን መስክረዋል። ኢሳያስ “ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም... በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው” (ኢሳ. 9:1-2) በማለት ኢየሱስ በጨለማ ላሉት፣ ለተጨነቁት፣ በሞት ጥላ ለኖሩት የሚያበራ ብርሃን እንደሆነ ምስክሯል። ይህ ብርሃን ለኛ ሰው ሆኖ የተወለደልን እንደ እግዚአብሔር ልጅ ደግም የተሰጠን፣ አለቅነት ለዘላለም በጫንቃው ላይ የሆነው፣ ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ብለን የምንጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ቁ. 6)። ማቴዎስ ኢሳያስን ጠቅሶ በሞት ጥላና በጨለማ ለተቀመጠ ሕዝብ የሚያበራ “ታላቅ ብርሃን” ይለዋል(4:14-16)። በሉቃስ ወንጌል ይህ ኢየሱስ “ከላይ የመጣ ብርሃን”፣ “በሞትና በጨለማ ላይ የሚያበራ ብርሃን” ደግሞም “ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን” ተብሏል (1:78-79፤ 2:32)። ዮሐንስ በወንጌሉ “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን” ይለዋል (1:9)። ለዋሪያው ጳውሎስ ከፀሃይ ብሩህነት የበለጠ የሚያበራ ብርሃን ሆኖ ተገለጠለት (ሐዋ. 26:13)። ዮሐንስ በክብሩ ሲያየው ፊቱ እንደ ፀሃይ ያበራ ነበርና በፊቱ መቆም አልቻለም። ወደ እኛ የመጣው ሰማያዊ ብርሃን ተጨንቀው ላሉ፣ በጨለማ ላሉ፣ በሞት ጥላ ለተቀመጡ የሚያበራ፤ ደስታን የሚሰጥ፣ የአስጨናቂውን ዘንግ የሚሰብር ታላቅ ብርሃን ነው።
ወደ እኛ የመጣው ጌታ ብርሃን ነው። በጨለማ ላለች አለም ብርሃን ሆኖ መጣ። ወገኖቼ የብርሃን ምንጭ አንድ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ብቻ ነው በራሱ ብርሃን የሆነ። ብርሃን የሚወጣው፣ በጨለማው ላይ በቃሉ ለማብራት ስልጣን ካለው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። በዘፍጥረት 1:1-3 እንደምናነበው “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” (ቁ.1)። ነገር ግን እግዚአብሔር ከፈጠራት በኋላ (ምናልባትም ከሰይጣን መጣል ጋር ሳይገኛኝ አይቀርም) ምድር “ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ...” (ቁ.2)። በዚህች ባዶ በነበረችው፣ አንዳች ባልነበረባት፣ በጨለማ ተውጣ ለነበረች ምድር እግዚአብሔር መጥቶ ቃልን ተናገረ። እግዚአብሔር “ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ” (ቁ.3)። የግዚአብሔር ቃል ጨለማን የሚገፍ ነው። እግዚአሔር ሲናገር ጨለማው ከምድር ላይ ለቀቀ። ብርሃን የሆነው ፀሃይና ጨረቃ ስለተፈጠሩ ሳይሆን እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን ስላለ ነው። ቃል በሆነው በክርስቶስም በኃጢያት ጨለማ ላለች አለም ብርሃን ይሁን አለ። ብርሃንም ሆነ። እናም በሞት ጥላ ያሉ፣ ተስፋን የቆረጡ ብርሃን ወጣላቸው።እርሱ የሕይወት ብርሃን ነውና በክርስቶስ ያሉ በብርሃን እንጂ በጨላማ ደይደሉም። እግዚአብሔር በጨለማችን ላይ “ብርሃን ይብራ” ስላለ ጨለማችን በርቷል።