እግዚአብሔር እረኛዬ ነው -- በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ።
በመዝሙር 23 ንጉስ ዳዊት እግዚአብሔር በጠላቶቹ ፊት ለፊት ገበታን በፊቱ እንዳዘጋጀለት ይዘምራል። ገበታ ሁለት ነገሮችን ያመለክታል። አንደኛ ገበታ መክበርን ማሳያ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ የወዳጅነት መገለጫ ነው። በዚህ ስፍራ ዳዊት እግዚአብሔርን ትልቅ ግብዣ እንዳዘጋጀና ወዳጁን እንደጋበዙ አስተናጋጅ ያስበዋል። እንደሚታወቀው ገበታ የሚዘጋጀው ድግስ ሲኖር ነው:: ድግስ ደግሞ የሚኖረው አንድም የከበረን እንግዳ ለማስተናገድ ነው ወይንም ደግሞ የከበረ በዓልን ለመዘከር ነው። በዚህ ክፍል ግን የምናየው ገበታ የተዘጋጀው የነገስታት ንጉስ፤ የጌቶች ጌታ በሆነው ልዑል እግዚአብሔር ሲሆን በገበታው የታደመው ደግሞ እግዚአብሔር ከመሬት አንስቶ ያከበረው ሰው ዳዊት ነው። ስለዚህም ዘአምሪው ተደንቆ በረከቱን በመቁጠር እግዚአብሔርን ያመሰግናል።
ከላይ እንዳልነው በገበታ መታደም መክበርን ያመለክታል። ዳዊት በዚህ ክፍል የሚቀኘው እግዚአብሔር እንዴት እንዳከበረው ነው። በእርግጥም እግዚአብሔር ዳዊትን አክብሮታል። አባቱ እሰይ በረሳው ጊዜ እንኳን እግዚአብሔር አስቦታል። የእስራኤልን ተግድሮት በእጁ ላይ ጥሎ በሞገስ ከፍ ክፍ አድርጎታል። የሳኦል ቁጣ በላዩ ላይ ነዶ በኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ቀርቷል ባለበት ሁኔታ ጣልቃ እየገባ አድኖታል። በዘላለም ኪዳን የፀና መንግስትን ሰጥቶትል። ስለዚህም ዳዊት የሚዘምረው እግዚአብሔር ሆይ ባንተ ከብሬአለሁ እያለ ነው። በእርግጥም እግዚአብሔር የሚያከብር አምላክ ነው። ሰው በኃጢያት ምክንያት የጎደለው ከእግዚአብሔር ክብር ነው። ለዚህም ነው ቃሉ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋ” (ሮሜ 3:23) የሚለን። በክርስቶስ ደግሞ እግዚአብሔር መልሶ ወደ ክብር አግብቶናል። ይህንንም ቃሉ “አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው” (ሮሜ 8:30) በማለት ያረጋግጥልናል። እግዚአብሔር አክብሮናል።
እንዲሁም ደግም ገበታ የሚዘጋጀው ለወዳጅ ነው። ዳዊት እግዚአብሔር በፊቴ ገበታን አዘጋጅቶልኛል ሲል እየገለጸ ያለው እግዚአብሔር ወዳጁ እንደሆነ ነው። አብረሃም ለእግዚአብሔር የቀረበ፤ እግዚአብሔርም ለአብረሃም የቀረበ ስለነበረ አብረሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተብሎ ተጠራ (2 ዜና. 20፡ 7፤ ያዕ. 2:23)። እንዲሁም ጌታ ኢየሱስ እኛን “ወዳጆች” ብሎ ይጠራናል (ዮሐ. 15:15)። እግዚአብሔር ስለወደደን በፊታችን ገበታን አዘጋጅቶልናል። ስንቀበለው እንደ ወዳጅ (ከወዳጅም የቀረበ) ሕብረትን ከኛ ጋር ያደርጋል። ለዚህ ነው ጌታ በቃሉ “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” በማለት ይህንን አስደናቂ ሕብረት የገለጸልን (ራዕ. 3:20)። አብሮ እራት መብላት እጅግ መቀራረብንና ወዳጅነትን የሚገልጽ ነው። ጌታ ከኛ ጋር እራት ይበላል። የተጠራነው ወደዚህ አስደናቂ የከበረ ሕብረት ነው። እንዲሁም ደግሞ ቃሉ “ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው” እምደሚል በመጨረሻም በበጉ ሰርግ እራት ላይ እንታደማለን (ራዕ. 19:9)።
ወገኖቼ፦ እግዚአብሔር ይህንን ክብር ያዘጋጀልን ጠላታችን እያየ (በጠላታችን ፊት) ነው። ጠላታችን ሁል ጊዜ በዙሪአችን ሊዞረን ይችላል። ነገር ግን የጠላት በዙሪያችን መኖር በኛ ላይ የሚገለጠውን የእግዚአብሔርን ክብር ሊከለክል አይችልም። እንዲሁም በጠላታችን ፊት ለእራት መታደም በእግዚአብሔር ያለንን የማይናወጥ ሰላም የሚገልጽ ነው። እእግዚአብሔር ስለ ወደደን አክብሮናል። ስሙ ለዘላለም የተባረከ ይሁን። አሜን!