top of page

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው -- በእግዚአብሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።

የእግዚአብሔር እረኝነት በምድር በሚኖረን ሕይወት በሚገለጠው የእርሱ መግቦት፣ ጥበቃ፣ መሪነትና ባርኮት ብቻ የሚገለጥ ሳይሆን የዘላለምን ተስፋ የሚሰጥ ነው። ለዚህ ነው ዳዊት በመዝሙር 23 መደምደሚያ ላይ “በእግዚአብሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ” በማለት የዘመረው። ጌታችንም እርሱ እውነተኛ የበጎች እረኛ እንደሆነ አስተምሮ “እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም” በማለት ከርሱ ጋር ለዘላለም በሕይወት እንደምንኖር የጸና የተስፋ ቃል ሰጥቶናል (ዮሐ. 10:28)።

መጽሐፍ ቅዱሳችን ይህንን ተስፋ በተደጋጋሚ በመግለጽ ያጽናናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምድር አገልግሎቱን ጨርሶ ወደ መስቀል ከመሄዱ በፊት “ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ. 14:2-3) በማለት ለዘላለም ከርሱ ጋር እንደሚሆኑ በማሳሰብ ደቀ መዛሙርቱን አጽናናቸው። በዚህ ስፍራ ጌታ በመለየቱ አዝነው ለቆዘሙት ደቀ መዛሙርት “ልባችሁ አይታወክ” እያለ ያጽናናቸዋል። እንደ ክርስቲያኖች በማንኛውም ሁኔታ መታወክ የለብንም። ይልቁንም ቃሉ እንደሚያስተምረን በመታወክ ፋንታ ማመን ነው ያለብን። ጌታ “በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ” እንዳለ እግዚአብሔር ነገርን ሁሉ እንደሚቆጣጠር እንዲሁም ምንም ከርሱ የተሰወረ ነገር እንደሌለ በማመን መመላለስ አለብን። ጌታችን የዘላለምን ስፍራ (ቤት) በእርሱ ዘንድ እንደሚያዘጋጅልን ቃል ሰጥቶናል። ይህንን የዘላለም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር የታመነ ነው።

እኛ ተስፋችን ከምድር ወይንም ምድራዊ አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ [ያለውን] እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም” (ቆላ. 3:1-2) እንደሚል አሳባችን እና መሻታችን መሆን ያለበት በላይ ያለው (ሰማያዊው) ነው። በላይ ያለው የዘላለም ነው። በምድር ያለው ጊዚያዊ እና የሚጠፋ ነው። የምድር ሕይወታችን እንኳ “ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት” ነው። አሁን ያለነው በድንኳን ነው። ነገር ግን “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለን” (2ቆሮ. 5:1)። ስለዚህ አሁን ከብዶን የምንቃትትበት ድንኳን ሲፈርስ ከሰማይም የሚሆነውን የዘላለሙን መኖሪያችንን እንለብሳለን። ስለዚህም መጽሐፍ “በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን” በማለት እንደሚገስጸን ለኛ በክርስቶስ ላመንነው የተጠበቀለን ታላቅ የሆነ የዘላለም ትንሳኤ ተስፋ አለን።

ወገኖች፦ ዘማሪው ዳዊት ምንም እንኳ በምድር የተከናወነ ጦረኛ፣ በሞገስ የጠገበ ዝነኛ፣ የከበረ ባለጠጋ፣ የተቀባ ንጉስ ቢሆንም ተስፋው ግን ምድራዊ ብቻ አልነበረም። ከምድር አሻግሮ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠበቀለትን የዘላለም ርስት በማሰብ “በእግዚአብሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ” በማለት በእመነት ተሞልቶ በሃሴት ዘመረ። እኛም ከምንም ነገር በላይ አንድ ቀን ጌታችን ፊት ለፊት እንደምናየው፤ ለዘላለም ከእርሱ ጋር እንደምንሆን እያሰብን ልባችንን በሰማያዊው ተስፋ ላይ አድርገን፤ የዘላለም ርስታችንን እያሰብን በእምነትና በሃሴት መመላለስ አለብን። በእምነት ጸንተን ጌታን ስናየው “ያን ቀን” እርሱ የዘላለምን የጽድቅ አክሊል ያስረክበናል። የጌታ ስም ለዘላለም የተባረከ ይሁን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page