top of page

የእምነት አቋም

1. እግዚአብሔር

       

 እውነተኛ አምላክ በሆነው፤ ለዘላለም በክብርና በስልጣን እኩል በሆኑ በሶስት አካል በሚኖረው በእግዚአብሔር አብ፣ በእግዚአብሔር ወልድና በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ እናምናለን። (ማቴዎስ 28፡ 19-20፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡14)

 

እግዚአብሔር መላውን አለም እንደፈጠረና ሰውንም በአምሳሉ እንዳበጀ እናምናለን።

(ራዕይ 4፡11፣ ዘፍጥረት 1፡26)

ከሥላሴ አካል አንዱ የሆነው ጌታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደተወለደ እናምናለን። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ወልድ እንደሆነ፣ ሙሉ ሰው ሙሉም አምላክ መሆኑን፤ በምድር አገልግሎቱ ለለ እግዚአብሔር መንግስት መስበኩን፣ ለሰው ልጆች የኃጢያት ዕዳ በመስቀል እንደተሰቃየና እንደሞተ፣

እንደተቀበረም፣ በአካልም ከሙታን እንደተነሳ፣ ለሰዎችም እንደታየ፣ ወደ ሰማይም

እንዳረገ፣ አሁን በአብ ቀኝ ተቀምጦ ለእኛ እንደሚማልድና፣ በታልቅ ኃይልና ክብርም

ተምልሶ እንደሚመጣ እናምናለን። (ዮሐንስ 1፡1፣ ፊልጵስዩስ 2፡6፣ ዮሐንስ 14፡9፣

ኢሳያስ 7፡12፣ ሉቃስ 1፡30፣ ዕብራውያን 4፡6፣ 1 ቆሮንቶስ 15፡3-8፣ 1 ጢሞቴዎስ

2፡5፣ 3፡16፣ ሮሜ 3፡24-25፣ ማርቆስ 16፡19፣ የሐዋርያት ስራ 1፡9፣11፣ 10-

42፣ ራዕይ 1፡7-20፣ 22፡12፣ 1 ተሰሎንቄ 2፡16፣ 4፡15-17፣ ዮሐንስ 1፡10)

ከሥላሴ አካል እንዱ የሆነው መንፈስ ቅዱስ አምላክ እንደሆነና በአብና በወልድ ያሉት

ባህሪያት ሁሉ እንዳሉት እናምናለን። ሰዎች በኢየሱስ ሲያምኑ መንፈስ ቅዱስ ዳግም ልደትን እንደሚሰጥ፣ የደህንነትን ማረጋገጫ እንደሚያትምና ሰዎች የክርስቶስ አካል እንዲሆኑ እንደሚያደርግ እናምናለን። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ እንደሆነ፣ የቀደሙትን ነብያትንና ሐዋሪያትን ያነቃቃ እንደነበረ፣ አሁን ደግሞ በውስጣችን በመሆን ኃይልን እንደሚሰጠንና ቤተ ክርስቲያንም ትታነጽ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለአማኞች እንደሚያከፋፍል፤ ዓለምንም ስለ ኃጢያት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ እንደሚወቅስ እናምናለን። (ዮሐንስ 14፡26፣ 2 ጴጥሮስ 1፡21፣ የሐዋርያት ስራ 1፡8፣ 1 ቆሮንቶስ 12፡4-11፣ ኤፌሶን 4፡11-12፣ ዮሐንስ 16፡8)

 

2. መጽሐፍ ቅዱስ

         ስልሳ ስድስቱ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን መጽሐፍትን የሚጠቀልለው መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ነጂነት ለሰው የሰጠው መገለጥ እንደሆነ እናምናለን።

መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት የሌለበት፣ ብቸኛ፣ ፍጹም፣ የበላይና የመጨረሻ የእምነትና

የሕይወት መመሪያ እንደሆነ እናምናለን። (2ኛ ጴጥሮስ 1፡21፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16፤

ሮሜ 15፡4፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡11 እና 1ኛ ተሰሎንቄ 2፡13)

 

3. ድነት

         ሰው በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠረ ነገር ግን በፈቃዱ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍ በኃጢያት እንደወደቀና ከዚህም የተነሳ ሰው ሁሉ በኃጢያት ባርነት ስር እንዳለ፣ ኃጢያቱን የሚናዘዝና ጌታ ኢየሱስ ክርቶስን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ የሚቀበል ሁሉ ዳግመኛ ከመንፈስ ቅዱስ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን እንደሚችል እናምናለን። ድነት በስራ ሳይሆን በጸጋ በእምነት ከእግዚአብሔር የሚገኝ እንደሆነ እናምናለን። (ማቴዎስ 1፡21፣ ሉቃስ 1፡68-69፣ ዮሐንስ 1፡11-14፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17፣ ሮሜ 3፡23-25፣ 1 ቆሮንቶስ 1፡30-31፣ ሮሜ 8፡29-30፣ ገላቲያ 6፡15፣ ኤፊሶን 1፡17፣

4፡11-16፣ ዕብራውያን 2፡10፣ 1 ጴጥሮስ 5፡10)

 

4. ቤተ ክርስቲያን

          ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ አንድ አካል ይሆኑ ዘንድ የተጠመቁ አማኞች ስብስብ እንደሆነችና አላማዋም ራሷ ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መመስከርና ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ መስበክ እንደሆነ እናምናለን። የቤተ ክርስቲያን ራስ ጌታ ኢየሱስ እንደሆነ እናምናለን። (የሐዋርያት ስራ 2፡41፣ 15፡ 13-17፣ ኤፊሶን 1፡3-6፣ 1 ቆሮንቶስ 12፡ 12-13፣ማቴዎስ 18፣ ኤፌሶን 5)

 

5. የውሃ ጥምቀት

          ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛቸው የተቀበሉ ሁሉ በውሃ ጥምቀት ሰነ-ስረዓት ከጌታ ኢየሱስ ጋር ለዓለም መሞታቸውንና ከእርሱም ጋር መነሳታቸውን በገሃድ እንደሚመሰክሩ እናምናለን። (ማቴዎስ 28፡ 19-20፣ ማርቆስ 16፡16፣ የሐዋርያት ስራ 10፡ 47- 48፣  ሮሜ 6፡1-4)

 

6. የጌታ እራት

            እንጀራን በመቁረስና ጽዋን በመካፈል የምንፈጽመው የጌታ እራት ስነ-ስረዓት የመለኮት ባህሪ ተካፋይነታችንን የምንገልጽበትና የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይና ሞት የምናስብበት ስነ-ስረዓት እንደሆነ እናምናለን። (2 ጴጥሮስ 1፡4፣ 1 ቆርንቶስ 11፡23-26፣ ሉቃስ 22፡19-20)

 

7. የቅድስና ኑሮ

           ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል በመታዘዝ ለእግዚአብሔር የተለየ ኑሮ በመኖርና ፍሬን በማፍራት ጌታን ለማክበር እንደተጠሩ እናምናለን። (ያዕቆብ 1፡22-25፣ ሉቃስ8፡8፣15፣ 2ኛ ጢሞቲዎስ 2፡19፣ ዕብራውያን 12፡14፣ 1ኛ ጴጥሮስ 1፡15-16፣

ገላቲያ 5፡22-24፣ 1ዮሐንስ 2፡6)

 

8. ዳግም ምጽአት

            ሰዎች ሁሉ እያዩት ወደ ሰማይ ወደ አብ ቀኝ ያረገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በግልጽ በክብር ወደ ምድር እንደሚመለስ እናምናለን። ኢየሱስ ዳግም ሲመለስ በክርስቶስ የሞቱት ቅዱሳን ሁሉ ትንሳኤን አግኝተው በእርሱ የምናምን ሁሉ በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር እንደምንኖር እናምናለን። እግዚአብሔርን ያልታዘዙና በኢየሱስ ያላመኑ ሁሉ እንደሚፈረድባቸውና ወደ ዘላለም ሞት እንደሚሄዱ እናምናለን (ማቴዎስ 25፡ 34-46፣ ሉቃስ 12፡40፣ ቲቶ 2፡13፣ ዕብራውያን 9፡27፣ ራዕይ 20፡1-7፣ 10-15፣

19፡11-14)

bottom of page