ኢየሱስ ይወዶታል!
አንባቢ ሆይ:- ይህች ጽሑፍ በአጋጣሚ ወደ እርሶ አልደረሰችም። ይህችን ጽሑፍ ያገኙት እግዚአብሔር ለርሶ አስደናቂ የፍቅር መልዕክት ስላለው ነው። እግዚአብሔር ይወዶታል። ፍቅር ጥልቅ ነገር ነው። ብዙ ጊዜ አንረዳውም ነገር ግን እንለማመደዋለን። ፍቅር አያስገድድም ነገር ግን ብርቱ ገፊ ነው። ከያኒያን ዜማን ከግጥም አዋህደው፤ ቀለም በቡርሽ አጣቅሰው፤ ድርሰት ከምናብ አፍልቀውና ምስል ከድምጽ አቀናብረው ስለ ፍቅር ጥልቀት፣ ጥንካሬና ውበት ይቀኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስም የፍቅርን ኃይል ሲገልጽ “ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና … ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም” ይላል። (መኃ 8፡ 6-7) እግዚአብሔርም ሰውን የወደደበት ፍቅር እጅግ ብርቱና ጥልቅ ነው። እግዚአብሔር አንድ ልጁን ለመስቀል ሞት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ሰውን ሁሉ ወዷል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ፍቅር “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት ይገልጸዋል (ዮሐ. 3፡16) ይህ ፍቅር እርሶንም የሚጠቀልል ነው። እግዚአብሔር እኛ በሕይወት እንኖር ዘንድ ሃጢያት የማያውቀውን አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለኛ በደል በመስቀል እንዲደቅና እንዲሞት በመፍቀድ ለእኛ ያለውን ወሰን የሌለውን ፍቅሩን አሳይቷል። አንባቢ ሆይ:- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል የሞተው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የለየውን የኃጢያት ግድግዳ በሞቱ አፍርሶ ለሚያምን ሁሉ የሚሆን የደህንነትን መንገድ ለማበጀት ነው። እግዚአብሔር ሰውን በምሳሌው ፈጥሮ እንዲበዛና ምድርን እንዲሞላት፣ ምድርንም እንዲገዛና እንዲያስተዳድር ባርኮት፣ ከእርሱም ጋር ሕብረትን እያደረገ በገነት እንዲኖር በክብር ስፍራ አስቀምጦት ነበር። ነገር ግን ሰው በዲያቢሎስ ተንኮል ተታሎ የፈጣሪውን ትዕዛዝ በመተላለፍ መንፈሳዊ ሞትን ሞተ። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ኃጢያት ገባ። ከዚያም በኋላ የተከተለው የአዳም ትውልድ ሁሉ በኃጢያት ስር ወደቀ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” ይለናል። (ሮሜ 3፡23) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ኃጢአት በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም ገባ። የኃጢያት ዋጋ ወይንም ውጤት ሞት ሰለሆነ በኃጢአትም በኩል ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ። አንባቢ ሆይ፦ ጌታችን ኢየሱስ ከቅድስት ድንግል ማሪያም ተወልዶ በመስቀል ላይ የሞተው በኃጢያት ምክንያት የመጣብንን የሞት ፍዳ ለመክፈል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የአለምን ኃጢያት ሁሉ ተሸክሞ በመስቀል ላይ በመዋል፣ ስጋው ተቆርሶ፣ ደሙ ፈሶ ለአለም ሁሉ የሚሆን የደህንነት ቤዛ ሆኗል። በክርቶስም መስቀል በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የለየው ኃጢያት፣ በኃጢያትም ምክንያት በሰው ላይ ነግሶ የነበረው ሞት ተነስቷል። እግዚአብሔር በባህሪው ፍጹም ጻዲቅ ፍጹምም መሃሪ በመሆኑ የክርስቶስ ሞት የኃጢያትን ቅጣት በመክፈል የእግዚአብሐርን ጽድቅ ፈጸመ። የክርስቶስ ትንሳዔ ደግሞ የእግዚአብሔርን ምህረትና የማዳን ኃይል በመግለጽ ሙታን ለነበርን ለኛ የድነት መንገድ ሆነ። ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነን በሞቱና በትንሳኤው ስንተባበር ለኃጢያት ሞተን ለጽድቅ ህያዋን እንሆናለን። አንባቢ ሆይ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የአለም መድኃኒት ነው። መድኃኒት እንዲፈውሰን እንድንወስደው ዘንድ እንደሚይስፈልገን ሁሉ፤ ከዘላለም ሞት እንድን ዘንድ ደግሞ ጌታ ኢየሱስን የግል አዳኛችን አድርገን እንድንቀበለው ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” በማለት ይህንን የደህንነት መንገድ ያረጋግጥልናል። (ዮሐ 1፡12) እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያዘጋጀው ብቸኛው የመዳን መንገድ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” በማለት ይመክረናል። (ሐዋ. 4፡12) ጌታ ኢየሱስም “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ይህንኑ አረጋግጦልናል። (ዮሐ. 14፡6) አንባቢ ሆይ፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሚል “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6፡23) ለደህንነት የሚያስፈልገውን ዋጋ ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍሎልናል። ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተው በኛ ፋንታና በኛ ምትክ ነው። እኛ መሞት ሲገባን እርሱ ሞተ። በእርግጥም እግዚአብሔር ገና ኃጢያተኞች እያለን ወዶናል። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” ይለናል። (ሮሜ 5፡8) እግዚአብሔር ታላቅ የፍቅር ግብዣ አድጎ እየጠራን ነው። የኛ ፋንታ ይህንን መድኃኒት ወስደን ከኃጢያት በሽታ መፈወስና የዘላለምን ሕይወት መቀበል ነው። ይህንን የመዳን ግብዣ ሳንቀበል በሞት ብንቀደም ግን እድል ፋንታችን የዘላለም ሞት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሲመክረን “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም” ይለናል። (ዮሐ. 3፡36) አንባቢ ሆይ፦ ዛሬ ለርሶ የመዳን ቀን ነው። ከሞት ወደ ሕይወት የማምለጫ ቀን ነው። ስለነገ አያውቁም። ነገ በእርሶ እጅ አይደለም። ዛሬ ሕይወትን ይምረጡ። ዛሬ ይህንን የፍቅር ግብዣ ይቀበሉ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኞ አድርገው ለመቀበል ከወሰኑ የሚከተለውን የንስሃ ጸሎት ይጸልዩ ዘንድ እናበረታታዎታለን። “እግዚአብሔር ሆይ ዛሬ የደህንነትን ወንጌል እንድሰማ እድልን ስለሰጠኽኝ አመሰግንሃለው። እኔ ኃጢያተኛ ሰው ነኝ። ዛሬ ከቅድስት ድንግል ማሪያም ተወልዶ ስለኔ ኃጢያት በመስቀል የሞተውን፣ በሶስተኛውም ቀን ከሞት የተነሳውን ልጅህን ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኜ አድርጌ እቀበላለሁ። በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከአጢያቴ ሁሉ አንጻኝ፤ ቀድሰኝ፤ ልጅህ አድርገኝ፤ በመንፈስ ቅዱስም ማህተም አትመኝ። ስላደረክልኝ ምሕረት አመሰግንሃለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም። አሜን!” ይህንን ከላይ የሰፈረውን ጸሎት በእምነት ከጸለዩ ዛሬ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ብረሃን ተሸጋግረዋል። ስለ ክርስትና ሕይወት የበለጠ መረጃ እንዲያግኙና ከሌሎች አማኞች ጋር ሕብረት እንዲያደርጉ በሚከተሉት አድራዎች ሊያገኙን ይችላሉ።
በስልክ፡ (773) 910-0485 (773) 865-6102 (773) 593-2134 (773) 556-5345
በአካል፡ እሑድ 1፡30 p.m. -- 4፡30 p.m. አርብ 7፡00 p.m. -- 9፡00 p.m. አድራሻ፡ Chicago Yemsrach Evangelical Church 4455 N. Seeley Avenue Chicago, IL 60625
ድረገጽ፡ www.yeec.org
የሬዲዮ ስርጭት (401) 283-6902 በመደወል ያዳምጡ። ያስታውሱ የመዳን ቀን ዛሬ ነው! እግዚአብሔር ይባርኮት