top of page

ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ውስጥ በጌታ መታመን

ዛሬ እንደሚታወቀው ግራ የሚያጋቡ ነገሮች በርክተዋል።ሁላችንም አሁን ባለው ሁኔታ ስለጤናችን፣ስለሥራችን፣ስለንግዶቻችን፣ ስለልጆቻችን፤ ስለቤተሰቦቻችንና ሰለጓደኞቻችን ከበፊቱ በበለጠ እናስባለን። ግራ የሚያጋቡ ነገሮች መኖራቸው ሁሌም የማይቀር ቢሆንም ምናልባት የአሁኑ ጫን ብሎ የመጣ የዘመናችን ልዩ ክስተት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።ነገር ግን በዚህ ክፉ ጊዜ አእምሮአችን የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ፊትለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ ኢየሱስን ከፍ በማደርግና ነብሳችንም በምታተርፍበት መንገድ ለመመለስ መሞከር ያስፈልጋል። ደግሞም የሚረዳ ጸጋም ተሰጥቶናል።

አንድ ወቅት አንድ የማያምን ሰው የበጎ አድራጎት ስራ ለመስራት ከአሜሪካ ወደ ህንድ አገር ይሄዳል። የሄደበት ዋንኛ አላማ ለወደፊት ህይወቱ አቅጣጫ ፍለጋ ነበር። እዛም በደረሰ በማግስቱ ማዘር ቴሬሳን ያገኛቸዋል። እሳቸውም በተለመደ ትህትና በተሞላው ሁኔታ “ወንድሜ ምን ላድረግልህ?” ብለው ይጠይቁታል። እርሱም እድሉን እንዳገኘ ምንም ሳያቅማማ እንዲጸሊዪለት ይጠይቃቸዋል።

ማዘር ቴሬሳም መልሰው በምን ርዕስ ወይንም በምን ሀሳብ ላይ ልጸልይህ ብለው ይጠይቁታል።እርሱም በሺዎች የሚቆጠሩ ማይሎችን አቋርጬ የመጣሁት ለህይወቴ አቅጣጫ ለመፈለግ ነው። ጥርት ያለ አቅጣጫ በህይወቴ እንዲኖረኝ ስለምፈልግ ጸልዩልኝ ይላቸዋል።

ማዘር ቴሬሳም ፈጠን ብለው “አይሆንም! በዚህ ሀሳብማ አልጸልይልህም። እርሱንማ ተወው ማንም አቅጣጫውን ጥርት አድርጎ ሊያውቀው አይችልም ይሉታል።” እርሱም አገር አቋርጬ የመጣሁት ጥርት ያለ አቅጣጫ ለመፈለግና ያንንም ከማዘር ቴሬሳ ለመማርና ለመረዳት ነበር ብሎ በድንጋጤ ተሞልቶ ያያቸዋል። ማዘር ቴሬዛም ፈገግ እያሉ “አንድም ቀን ጥርት ያለ አቅጣጫ በህይወቴ ኖሮኝ አያውቅም ነገር ግን ሁሌም አንድ ነገር አውቃለሁ ይሄውም በእግዚአብሄር መታመን ነው።እርሱ ሁሌም አለኝ፤ በእርሱ ሁሌም እታመናለሁ፤ የማደረገው ነገር ሁሉ በእርሱ ታምኜ አደርጋለሁ በዚህም ምክንያት የራሴ የሆነ የተለየ አቅጣጫ ኖሮኝ አያውቅም አሉት። ከዛም ማዜር ቴሬሳም በተማጽኖ መልክ አይናቸውን ወደእርሱ አንስተው በእግዚአብሄር እንዲያምንና እንዲታመን ፈቃደኛ ከሆነ እንደሚጸልይዩለት አሳወቁት።

ሁሌም ጥርት ያለ አቅጣጫ የምንፈልግባቸው ነገሮች ጠፍተውብን አያውቁም። ከአዳማዊ ባህሪያችንና ከአለመረጋጋታችን የተነሳ ሁሌም አቅጣጫ እንፈልጋለን። አቅጣጫ የማወቅ ፍላጎታችንም እየጠነከረ ሲሄድ በውስጠ ታዋቂነት በእግዚአብሄር ያለንን መደገፍ ለመተካት የሚደረግ ሩጫም አካል ሊሆን ይችላል። በአብዛኛውን ጊዜ ከፊትለፊታችን ያለውን አቅጣጫ በግልጽና በዝርዝር ለማወቅ ከመኳተን ይልቅ ጥብቅ ቁርኝት ከእግዚአብሄር ጋር ብናደርግ እርምጃችን የተስተካከለ ይሆናል። ወደ ተፈለገውና ትክክል ወደሆነው አቅጣጫም ይመራናል። በእርግጥ እርሱ የአስር አመት ፍኖተ ካርታ ሊሰጠን ቃል አልገባልንም። አንዳንዴ አቅጣጫ ብቻ መፈለግ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያመጣብን ይችላል። በእግዚአንሄር ያለንን መታመን ማለትም በእምነት ያገኘነውን መተማመንና እለት በእለት በእርሱ ያለንን መደገፍ ሊያደበዝዝም ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱሳችን በመዝሙር 62፤8 እንዲህ ይላል “አለቴና መድኀኒቴ እርሱ ነው፤መጠጊያየም እርሱ ነው፤ከቶ አልናውጥም።” ስለዚህ ልባችንና በውስጡ የታጨቁትን፤አምልኮም፣ምስጋናም፣ጭነቀትም፣፣ጥርጣሬም፣ፍርሀትም ቢሆን ወደ እርሱ ማፍሰስ ነው ያለብን። ስለዚህ ሁል ጊዜ ልንታመንበት ይገባል እንጂ ሁሉም ነገር አይነካኝም ብሎ ማሰብም አያስፈልግም።

አቅጣጫ ሲደበዝዝና ሲጠፋ በአብዛኛውን ጊዜ እምነታችን ከፍ ይላል።ኖህ መርከቡን የሰራው 120 አመትታን በሙሉ ድንገት ይመጣል የተባለውን ዶፍ ዝናብ እያሰበ ነበር። ሳራም ልጅ እንደምትወልድ በእግዚአብሄር የታመነችው በስተርጅና ነበር።አብርሀምም በእምነት አንድ ልጁን ለእግዚአብሄር ለመሰዋእት ሊያቅርብ የወጣው በእግዚአብሄር በመታመን ነበር። እጅግ ብዙ ከበድ ያሉ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል። እውነት ግን ሁሌም እውነት ነው። እምነታችን እንደ አደይ አበባ ፈክቶና ጎልቶ የሚወጣው በእግዚአብሄር በጽኑ በመታመን እንጂ በግላችን አቅጣጫ ለመፈለግ በምናደገውን ሩጫ አይደለም።

ሁሌም አቅጣጫችንን ለመቀየሰ እንጨነቃለን ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚለን በመንፈስ እንድንመራ ነው።እኛ በፍኖተ ካርታ ለመመራት እንጥራለን ነገር ግን እየሱስ የሚለን “ተከተሉኝ” ነው። ሁሌም ለጥያቄዎቻችን መልሶች እንፈልጋለን ነገር ግን እግዚአብሄር በእኔ ታመኑ ነው የሚለን ።

ስለዚህ የነገሮችን የምናይበትን መነጽር በማስተዋል መመርመር መልካም ነው። ኒውዮርክ እንዲህ ስለሆነ፤ካሊፎርኒያ እንዲያ ሰለሆነ ሳይሆን፤ሉዚያና ጫን ያለ ስለሆነ፤ነብራስካ ጥቂት ስለሚታይ ሳይሆን፤መዝሙረኛው እንዳለው “አምላካችን መጠጊያችንና ኅይላችን ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችህን ነው ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” እያልን እኛም የተቀደሱ እጆቻንን ወደ እርሱ እናነሳለን እርሱም ያድነናል!!!!!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page