top of page

እንዲጋረድ የተፈለገው የቀስተ-ደመናው ትርጓሜ፤ እና የአማኝ ሃላፊነት

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በምእራቡ አለምና በሃገራችን በኢትዮጲያ በተወሰነ መልኩ በትምህርት ቤቶች፣ በአንዳንድ ቢሮዎች፣ በቤትና በአፓርትመንት መስኮቶች ላይ በወረቀት የተቀለመ ህብረቀለማትን አዋህዶ የያዘ የቀስተ-ደመና ቀለማት ቅጂ መመልከቱ እየተለመደ መጥቱዋል፡፡

የሰው ልጅ እግዚአብሄር የፈጠረውን ተፈጥሮ ባልተለመደና አላማውን በሳተ፣ ለህሊና በሚከብድ እና በሚያጸይፍ መልኩ ቀይሮ መጠቀሙ በታሪክ ምእራፍ ውስጥ በተለያየ ግዚያት ሲደጋገም ይታያል፡፡ የአመጽ ልጅ የሆነው ሃሰተኛው ዲያቢሎሥ አግዚአብሔር የፈጠረውን እና የሰራውን ኮፒ በማድረግ ለረከሰ ዓለማ እና ተግባር ማዋሉ ሔዋን እና አዳምን በገነት ከማሳቱ አስቀድሞ ሢሦ ያክሉን ማላእክት አስቶ ወደ ምድር የተጣለ ጊዜ የጀመረ እና እሰከ ዘመነ- ፍጻሜው ማለትም እስከ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት እሰኪሆን ድረስ ብሎም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በፍርድ አስኪደመደም ድረስ ለጊዜው አንዳንዶቹን እያሳተ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

እግዚአብሔር በውሃ ሙላት ምድርን ላለማጥፋት ከኖህ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ፣ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውሃ አይጠፋም፣ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውሃ አይሆንም ብሎ በመጽሃፍ ቅዱስ ተናግሩዋል፤ ዘፍጥረት 9፡ 11-13 ይመልከቱ፡፡ ለዚህም ደግሞ የሚሆን ምድር በደመና በተጋረደ ጊዜ የቃል ኪዳን ምልክት የሆነው ቀስተ-ደመና በሰማይ እና በምድር መካከል እስከዛሬ ድረሥ ይታያል፡፡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መምህራን እነደሚናገሩት፤ ይህ የቀስተ-ደመና ምልክት እግዚአብሔር በክርስቶስ አየሱስ በኩል አለምን ሁሉ እንደሚቤዥ አመላካች እነደነበርና እነደሆነም ይስማማሉ፡፡

ዛሬ ላይ ይሄን የቃል-ኪዳን እውነት በተቃረነ መልኩ አምላክ ለፍጥረቱ ያቆመውን የቀስተ ደመና ምልክት ያለ ፈጣሪው ፈቃድ፣ እውቅና፣ በመኮረጅና በመቅዳት ፣ የእግዚአበሔርን የፍጥረት ሕግ ፍጹም በተጣረሰ መንገድ ለረከሰ አላማ እነዲውል ተደርጉዋል፡፡ የሐሰት አባት የሆነው ዲያብሎስ የተውሰኑትን በማሳት አእምሮአቸውን ቆልምሞ መጠቀሚያ መሳሪያው በማድረግ ጾታዊ ግንዛቤ (sexual orientation ) በሚለው ኢ-ፍጥረታዊ ሥልቱ (strategy) ትውልድን ሊበላ ጥርሶቹን አሹሎ ምልክቱንም የቀስተ-ደመና ቀለማት ቅጂ በማድረግ በጭካኔ ከተነሳ ሰነባብቱዋል፡፡ ለዚህ ተግባሩም ጾታዊ ግንዛቤ (sexual orientation) የሚለውን ትውልድ አጥፊ ትምህርት በለጋ ሕጻናት አእምሮ ውስጥ ለማስረጽ ከግብረ-አበረቹ ጋር በመሆን ደፋ-ቀና ሲል ይታያል፡፡ የተወሰኑትንም አስቶ በኃጥያት የጨቀየ ኩሬ ውስጥ በአረንቋ ተይዘው እንዲቅበዘበዙ በማድረግ ወደ ዘላለማዊ ሞት እያጃጀለ በመምራት ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከኃጥያት ለመመለስ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ለወደደ እና ለፈቀደ ለማንኛውም ሰው አሁንም የክርስቶስ ደም የጣራል፣ አልረፈደም ፣ ደጆቹም አልተዘጉም ክፍት ናቸው፡፡ ሆኖም ግን እያንዳንዱ ሠው እራሱን እና ትውልድን የመታደግ ኻላፊነት እንደወደቀበት መገንዘብ ይገባዋል፡፡ ይህን ኃላፊነት እንዴት መወጣት ይቻላል የሚለውን ጥያቄ ራሳችንን መጠየቅ አና ከንግግር ባለፈ ትውልድን ለሚታደግ ተግባር መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አውሬው ሎሌዎቹን ተጠቅሞ በአብዛኛው የአለም ክፍል የጾታ ግንዛቤ (sexual orientation) በሚል ሽፋንና ስልት ተጠቅሞ እጅግ መርዛማና ነፍሰ-ገዳይ የሆነው ግብረ-ሰዶማዊነትን በትውልድ መካከል ለማስፋፋት እየተራወጠ እና እየተሩዋራጠ ይገኛል፡፡ አካሔዱም ስልታዊና የረቀቀ መሆኑን መገነዘብ ግድ ይላል፡፡ በለስ ቀንቶት ብዙዎችን ከማሳቱ በፊት ይህን ወረርሽኝ መመከት ይቻል ዘንድ የሚጠቀምበትን ስልታዊ አካሄድ መገንዘቡ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም በትምሕርት ቤቶች ኣካባቢ በለጋ ሕጻናት አእምሮ ውሥጥ እየተዘራ ያለው የግብረ-ሰዶማዊነት ደዌ፣ ይሕ ዘላለማዊ ሕይወትን የሚቀጥፍ በሽታ እንደጤናማ ጾታዊ ትምህርት አማራጭ ተደርጎ መቅረቡ በመሃበራዊና ተፈጥሮአዊ ህይወታችን ላይ ሥጋትን ፈጥሯል።

በተጨማሪም የአዋቂ እና የህጻናትን አእምሮ ስልታዊ በሆነ አካሔድ ዲሴነሲታይዝ (ማለማመድ እና አቅልሎ ማሳየት) በማድረግ አውሬው መደበኛ በሆነ መንገድ እየሰራ እንዳለ አይን ያለው ማስተዋል ይችላል፡፡ እየተሰራጨ የሚገኘውን ግብረ-ሰዶማዊነት መግታት የሚቻልበት አንዱ መንገድ፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተና ትክክለኛውን የጾታ ትምህርት በማሥተማር ተተኪው ትውልድ ጤናማ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ነው፡፡ ለዚህም በቤትና በቤተ-ክርስቲያን በሚኖሩ ፕሮግራሞች ላይ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ጤናማ ትምህርት እንደእድሜያቸውና አቀባበላቸው ልክ በማስተማር፤ በህጻናት ሆነ በአዋቂዎች አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረጉ ለትውልድ ለሚቆረቆር አማኝ ከአስፈላጊነቱ ባለፈ ግዴታው እንደሆነ መገንዘቡ ተገቢ ነው፡፡

የቀስተ-ደመና ህብር የያዘውን ቅጂ በየትኛውም አጋጣሚ ስንመለከት፣ እግዚአብሔር ፍጥረትን በጥፋት ውሃ ዳግም ላለማጥፋት የገባውን ቃል-ኪዳን በማሰብ እና በማመስገን፣ ብሎም በዚያ ውስጥ እንዲተላለፍ የታሰበውን ኢ-ፍጥረታዊ የሆነ አስተሳሰብ መቃወም (reject) ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ፣ ክርስቲያናዊ ስረአተ- ትምህርት መቅረጽ፣ ጾታዊ ግንዛቤን በተመለከተ ጤናማና ወጥ የሆነ የማስተማሪያ ሰነድ (ዶክመንት) ማዘጋጀት፣ የተዘጋጀ ካለም ያን መፈተሽና መጠቀም መጀመርን ያካትታል፡፡ ክርስቲያናዊ ሥረአተ-ትምህርት ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት ህጻናት፣ወጣቶች እንዲሁም ኣዋቂዎች ሊገነዘቡት በሚችል መልኩ የሚቀርብ፤ አሁን ላይ በተለይም በአለማዊ(secular) ሥረአተ-ትምህርት ውስጥ ያለውን የተዛባ አስተሳሰብ የሚመረምርና የሚያርም፣ ያለንበትን ዓውድ (context) ያገናዘበና አብሮም የሚሔድ መሆን ይኖርበታል፡፡

የዚህ መቅሰፍት ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች ከሐጢያታቸው በመታቀብ ወደ እግዚአብሔር በንስሐ ቢመለሱ፤ ይቅር ሊላቸው ወደ መንግሰቱም ሊቀላቅላቸው ሁሌም ዝግጁ ነው፡፡ እንደአማኝ በተገኘው አጋጣሚ መንፈስ-ቅዱስ በመሚያሳስበንና ጥበብ በተሞላበት መንገድ ማሰተማር፣ ጤናማ ምልክቶችንና ጥቅሶችን በማዘጋጀት በቤቶቻችን፣ በመስኮቶቻችን፣ በተሽከርካሪዎቻችንና ሌሎች አመቺ በሆኑ ስፍራዎች ላይ በመለጠፍ፤ ቲሸርቶችን በማዘጋጀት፣ እግዚአብሄር ባሳሰበንና በሚከፍትልን የተለያዩ መድረኮች ተጠቅመን ለጽድቅ በሥራ እንቁም፤ ለእግዚአብሔር መንግስት መስፋትና ለትውልድ መዳን ምክንያት እንሁን፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ በጸሎትና በምልጃ እየተጋን በአሁኑ እና በመጪው ትውልድ ላይ ሥረአታዊና ስልታዊ በሆነ መንገድ እየተስፋፋ ያለውን የጾታ ግንዛቤ(sexual orientation) የሚል ጭምብል ያጠለቀ ግብረሰዶማዊነትንና መስፋፊያ መንገዱን፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ተፈጥሮአዊ በሆነ አስተምህሮት ሥልታዊ በሆነ መንገድ መጋፈጥ ከመቼውም በላይ አስፈላጌ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡ ሥለዚህም እንደ ግለሰብ፣ ቤተሠብ፣ እንደ ሐገር፣ እና አለም-አቀፋዊ ማሕበረሰብ በግልም ሆነ በቡድን ጥረታችንን አቀናጅተን እድሉ ሳያመልጠን በአንድነት መንፈስ ሆነን መታገል እንጀምር፡፡ ኃይልን በሚሠጠን በክርስቶስ ሁሉን እንደምንችል እያሰብን ለዚሁ የተቀደሰ አላማ እንትጋ፡፡

ክብር ለዓብ፤ ለወልድ እና ለመንፈሥ-ቅዱስ አንድ አምላክ ይሁን፡፡

አሜን


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page