top of page

ታላቅ ተስፋ

“ተስፋን ቃል የሰጠዉ የታመነ ነዉና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ። (ዕብ 10፡ 23)

ተስፋ ሰው በሕይወቱ እንደሚሆን በእርግጠኝነት የሚጠብቀው ነገር ነው። እያንዳንዱ ሰዉ ተስፋ የሚያደርገዉ ነገር አለዉ። በዚህች አጭር ጽሑፍ ለክርስቲያኖች (ለአማኞች) ተስፋ ምንድን ነዉ? ወደምን አይነት ተስፋ ነዉ የተጠራነዉ? የዚህ ተስፋ መሰረት እና ግብ ምንድን ነዉ? የኛስ ድርሻ ምንድን ነዉ? የሚሉትን ሃሳቦች እንመለከታለን። ተስፋ ቃል የተገባልን ነገር ገና ሳይፈጸም ማለት ነዉ። ተስፋ የእዉነተኛ እምነት ማረጋገጫ ነዉ። ተስፋ እንደምንቀበል፣ ወደፊት እንደሚሆን የምንጠብቀዉን ነገር በእምነት መጠባበቅ ነዉ። ተስፋ ቃል የተገባልን ነገር እዉነት እንደሆነ ማመን ነዉ። እንዲህ አይነቱ ተስፋ ሰዎች ባጠቃላይ በእለት-ተለት ሕይወት ከሚያወሩት ተስፋ ይለያል። እንዲህ አይነቱ ተስፋ ስለ አንድ ነገር ያለ ፍላጎት ብቻ አይደለም ነገር ግን በግዚአብሔር በራሱ ላይ እና በቃሉ ላይ መተማመን ማለት ነዉ።

ተስፋ የክርስቲያኖች ባህርይ ከሆኑትና ጸንተዉ ከሚኖሩት ከእምነት እና ፍቅር ጋር በተጓዳኝ የተቀመጠ ነው (1ቆሮ 13፡13)። የክርስቲያኖች የከበረ ተስፋ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥና ተመልሶ መምጣት ነዉ። የተስፋችን መሰረት ይህ ነዉ። ይህ ተስፋ ሕያዉ ተስፋ ነዉ፤ ዘላለማዊ ተስፋ ነው፤ የክብር ተስፋ ነዉ። ስለዚህ በ1ተሰ. 4 ፡18 ላይ “እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ” እንደተባልነው በዘመናት ሁሉ እርስ በእርሳችን በዚህ ተስፋ ልንጽናና ይገባል። በእርግጥ የክርስቶስ መመለስ ታላቅ የምንጽናናበት ተስፋችን ነዉ። እየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ ይመጣል።

ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚመለስ ድረስ አለም ፍጹም የመከራ ቦታ ሆና ትቀጥላለች (1ዮሓ5፡19)። ምክንያቱም አለም ሁሉ በክፉ እንደተያዘ ቃሉ ይነግረናል። (“በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ ይህን ነግረያችዋለሁ። በአለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ አለምን አሸንፌዋለሁ" (ዮሓ 16፡33)።) ተስፋችንን ስናስብና በተስፋ ስንጸና በዚህ ምድር በሚፈራረቁ መከራዎች እንዳንዝል ፤ ከባድም ቢሆን በመከራ ጊዜ እንድንታገስ አቅም ይሰጠናል። እንዲሁም በተስፋም እንድንደሰት ያስችለናል (ሮሜ12፡12)። ተስፋ ስናደርግ ጽናት እናገኛለን። ለሕይወታችንም አላማ ጽናት ይሰጠናል። በተመሳሳይም ሁልጊዜ የተዘጋጀ ሕይወት እንዲኖረን ይረዳናል። በ1ኛ ተሰ4 ፡13 ላይ “ነገር ግን ወንድሞችህ ሆይ ተስፋ እንደሌላቸው እንደሌሎች እንዳታዝኑ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን" እንደሚል የሞት ሃይል በትንሳዬ ሃይል ስለተሻረ በሞት ስለተለዩአቸዉ ወገኖች እንዳያዝኑ ለተሰሎንቄ ሰዎች ጳዉሎስ ስለዚህ ታላቅ ተስፋ ይጽፍላቸዋል። ይህ በዘመናት ሁሉ ላለን አማኞች ሁሉ ታላቅ መጽናኛ ነዉ።

ተስፋችን ታላቅ እና ህያዉ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱም ቅዱሳን ጌታ ሲመለስ ከርሱ ጋራ በታላቅ ክብር እንደሚመለሱ፤ ህያዉ ሆነዉ በምድር ያሉትም መለከት ሲነፋ በቅጽበት አይን ተለዉጠዉ ጌታን ባየር ለመቀበል እንደሚነጠቁ ያንቀላፉ እንጂ የሞቱ እንዳልሆኑ ይነግረናል። የሞት ኅይል ስለተሰበረ የስጋ ሞት ለክርስቲያን እንቅልፍ እንደሆነ እንድንረዳና ደስታችን እና መጽናናታችን በችግር ጊዜም የበዛ እንዲሆንልን ይህ ታላቅ ተስፋ ተሰጥቶናል። ጌታ እየሱስም “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” (ዮሓ14 ፡1 -3) በማለት ደቀ መዛሙርቱን አጽናናቸው። በዚያን ጊዜ የደቀመ መዛሙርቱ ልብ ተሸብሯል፤ ደግሞም ከጥቂት ጊዘ በኋላ የበለጠ ይሸበራል። ቀደም ሲል ተለይቶአቸዉ እንደሚሄድ ነግሮአቸዋል (ዮሓ13፡33)። ኢየሱስ በዚህ ክፍል ስፍራ እንደሚያዘጋጅልን፣ ተመልሶ ሊወስደን እንደሚመጣ፣ ከርሱም ጋራ ለዘላለም እንደምንኖርና በሚሆኑ ነገሮች ልባችን ሊታወክ እንደማይገባ ነግሮናል። ደግሞም በዚህ በሚደርስብን መከራ የሚያጽናናን ለዘላለም ከኛ ጋራ የሚኖር አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ተልኮልናል።

ይህ ቅዱሱ መንፈስ በመከራችን የሚያጽናናን ብቻ ሳይሆን በኤፌ1፡13 ላይ እንደተጻፈው የእግዚአብሔር ለመሆናችን የታተምንበት ማረጋገጫ ነው። እርሱም “ለክብሩም ምስጋና ለመሆን የእግዚአብሔር የሆኑትን እስኪዋጅ ድረስ እርሱ ለርስታችን ዋስትና የሚሆን መያዣ ነዉ።" መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ለመሆናችን ደግሞም ለዘላለማዊ ተስፋችን እና ርስታችን ማረጋገጫ ዋስትናችን ነዉ። ስለዚህ ወገኖች ሆይ የምንጽናናበት ታላቅ ተስፋ፤ ለዘላለም ከጌታ ጋራ የምንሆንበት ሀገር፤ ደግሞም ተመልሶ የሚመጣና የሚወስደን ጌታ እንዳለን እያሰበን እርስ በርስ እንጽናና ደግሞም ተስፋ እንደሌላችዉ በጠለቀ ሀዘን እንዳንዋጥ በተስፋችን ደስ ይበለን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page