top of page

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው -- ራሴን በዘይት ቀባህ።

መዝሙረኛው ዳዊት እግዚአብሔር እረኛዬ ስለሆነ እራሴን በዘይት ቀባኝ በማለት ይዘመራል። ዳዊት በተደጋጋሚ በእግዚአብሔር የተቀባ ሰው ነው። ገና በብላቴናነቱ እግዚአብሔር ሳዖልን የእስራኤል ንጉስ እንዳይሆን ከናቀው በኋላ ሳሙኤልን ቀንዱን በዘይት ሞልቶ ወደ እሰይ ቤት እንዲሄድ አዘዘው። ሳሙኤል ዘለግ ያሉትን የእሰይን ልጆች ሊቀባ ወዶ ነበር እግዚአብሔር ግን ሰው እንደሚያይ አያይምና ከሰባቱም የእሰይ ልጆች የሚቀባው አልተገኘም ነበር። ዳዊት የቀረ ልጅ የለም ወይ ተብሎ ተፈልጎ ከእረኝንቱ ስፍራ ተጠርቶ ተቀባ (1 ሳሙ. 16:13)። በመቀጠልም በይሁዳ ይነግስ ዘንድ ተቀባ (2 ሳሙ. 2:4)። ለሶስተኛ ጊዜም በእስራኤል ሁሉ ላይ ሲነግስ ተቀብቷል (2 ሳሙ. 5:3)። ዳዊት እረኛ በጎቹን በዘይት እንደሚቀባ ሁሉ መቀባቱን ከእግዚአብሔር እረኝነት ጋር አያይዞ ይዘምራል።

የዳዊት መቀባት የሚያሳየው ለንጉስነት መለየቱን ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስን አብሮነት ነው። በተለይም በአባቱ በእሰይ ቤት በተቀባ ጊዜ ይህንን ሃሳብ በቀጥታ እናገኘዋለን። የእግዚአብሔር ቃል “ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ” ይለናል (1 ሳሙ. 16:13)። ዳዎት መቀባቱን ተከትሎ ወዲያውኑ (“ከዚያን ቀን ጀምሮ”) በእርሱ ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ መጣ። ዳዊት ከዛ በኋላ የተመላለሰው በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ ከርሱ ጋር ስለነበር በሚያደርገው ነገር ሁሉ የተከናወነ ነበር። በእረኝነቱ ስራ ላይ በመንፈስ ኃይል ሆኖ በጎቹን ከጠላት እየነጠቀ ያድን ነበር። የተለየ የእግዚአብሔር ሞገስ በእርሱ ላይ ስለነበር የሳዖል አገልጋዮች እንኳን “መልካም አድርጎ በገና የሚመታ... ጽኑዕ ኃያል... በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ... እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር [የሆነ]” በማለት መስክረዋል። ይህ ሁሉ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ከመምጣቱ የተነሳ ነው።

በዘይት መቀባት ለእግዚአብሔር መለየትና በከበረ የእግዚአብሔ ሞገስ ውስጥ መሆንንም ያመለክታል። እግዚአብሔር በክህነት እንዲያገለግሉት ሌዊንና ልጆችን ሲለይ በከበረ ዘይት እንዲቀቡ አዘዘ። ይህ ቅባት በእግዚአብሔር ፊት ያማረና መልካም መአዛ ያለው ነው። ለዚህ ነው በመዝሙር 133 ላይ የወንድሞች ሕብረት በአሮን ራስ ላይ በሚፈሰው የከበረ ዘይት የተመሰለው። ይህ የቅባት ዘይት በአሮን ራስ ላይ ወርዶ፣ በጺሙ አልፎ በልብሱ መደረቢያ ላይ ይወርዳል። አሮን በሚያልፍበትም ሁሉ መአዛው ይወጣል። መዝሙረኛው “ራሴን በዘይት ቀባህ” እግዚአብሄር የሰጠውን በመንፈስ ቅዱስ የሆነውን የከበረ ሞገስ፣ ሃይልና ሕይወት የሚገልጽ ነው።

ወገኖቼ፦ እረኛችን እራስን በዘይት የሚቀባ ነው። ስለዚህ ነው በአዲስ ኪዳን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛል” (ሉቃ. 4:17) ያለው። አሁን ሁላችንም በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተናል። ስለዚህም ቃሉ “እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ” (1ዮሐ. 2:20) እንዲሁም “እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ” (1ዮሐ. 2:27) የሚለን። ከቅዱሱ ቅባት ተካፍለናል። እግዚአብሔር አምላክ በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተናል። ስለዚህም እንደ ዳዊት በሞገስና በኃይል እንዲሁም እንደ አሮን በተቀደሰ ሕይወት እድንኖር ተጠርተናል።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page