top of page

አስደናቂ ጸጋ!

“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ …እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።” (ዮሐ. 1፡14-17) ጁን 17 ቀን 2015 በሳውዝ ካሮላይና ቻርልስተን ከተማ ዳይለን ሩፍ የተባለ የ21 አመት ወጣት በኢማኑዔል አፍሪካን ሜትድስት ዔፕስቆጶስ ቤተ ክርስትቲያን በመግባት በጸሎት ላይ ከነበሩት አማኞች መካከል ዋናውን መጋቢ ጨምሮ ዘጠኙን በጅምላ ገደለ። ወንጀሉ በዘረኝነት ተነሳሽነት የተፈጸመ በመሆኑና አማኞች ቤተ ክርስቲያን እያሉ የተፈጸመ በመሆኑ ዜናው መላው አገሪቱን አናወጠ። የአሜሪካንን ሕዝብ በጣም ያስደመመው ግን የሟች ቤተ ሰቦች ላይ የታየው አስደናቂ ጸጋ ነበር። አንጀታቸው በሐዘን የተኮማተረ ቢሆንም ግድያውን የፈጸመውን ሰው ግን ይቅር ብለንሃል አሉት። ከዚህም የተነሳ ይመስላል በፓስተሩ የቀብር ሥነ-ስረዓት ላይ ተገኝተው የሃዘን ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኦባማ የንግግራቸውን ዋና ሃሳብ ያደረጉት አስደናቂ ጸጋ በሚል ሃሳብ ላይ ነበር። ፕሬዝዳንቱ በቅዱሳኑ ላይ የተገለጠው ጸጋ እጅግ ስላስገረማቸው ታዋቂውን “አስደናቂ ጸጋ” የተሰኘውን መዝሙር ከጉባዔውና ከተሰብሳቢው ጋር ዘምረዋል። ጆን ኒውተን የተቀኘው ይህ አስደናቂ ጸጋ የተሰኘው ዝማሬ በርግጥም በኢየሱስ ክርስቶስ ወደኛ የመጣውን ወደር የሌለውን ጸጋ ይገልጻል። የመዝሙሩ አንጓ እንዲህ ይላል፦ “አስደናቂ ጸጋ ድምጹ እንዴት ጣፋጭ ነው፤ እንደኔ ያለውን ብኩን ያዳነው፤ ጠፍቼ ነበር አሁን ተግንቻለሁ፤ እውር ነበርኩ አሁን ግን አያለሁ።” ጆን ኒውተን ይህንን ዝማሬ የተቀኘው በ1779 ነው። ነገር ግን ዝማሬው ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ በብዙ አማኞች ይዘመራል። መዝሙሩ የጸጋውን ጥልቀትና ሃይል ይገልጻል። መዝሙሩ ጸጋው እንዴት ከጨለማ ወደ አስደናቂው የጌታ ብረሃን እንደመጣን ይናገራል። መዝሙሩ ጸጋው እንዴት እለት እለት እንደሚረዳን ያበስራል። እውነትም አስደናቂ ጸጋ! ወገኖቼ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደኛ የመጣው ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ነው። ከዚህ ሙላት ደግም ሁላችንም ተቀብለናል። ወደኛ የመጣው የተትረፈረፈ ጸጋ ነው። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ “በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናል” የሚለን። በማንኛውም የህይወት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም፣ በከፍታና በዝቅታም — ሁልጊዜም ወደ ጌታ ዘወር ስንል ጸጋ አለ። በአንዱ ጸጋ ላይ ደግሞ ሌላ ጸጋ ይጨመራል። ሕጉ ፈጽሙ ይላል፤ ጸጋው ግን ተፈጽሟል ይላል። ሕጉ ወደ ላይ ውጡ ይላል፤ ጸጋው ግን ወደ ላይ ይስባል። ሕጉ ድካማችንን ያሳያል፤ ጸጋው ግን ድካማችንን ያግዛል። ሕጉ ይኮንናል፤ ጸጋው ግን ያጸድቃል። ወገኖቼ፦ የተሰጠን ጸጋ የሚያድን ጸጋ ነው። ደግምም በጽድቅ ለመኖር አቅምን የሚሰጥ ነው። እንግዲህ እንዲህ ያለ አስደነቂ ጸጋ ካለን ከኛ የሚጠበቀው እለት እለት ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት መቅረብና ጸጋውን መካፈል ነው።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page