top of page

ተባርከናል!

ተባርከናል! “በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።” (ኤፌ. 1፡3) ምድራዊ ሕይወት በረከትን ለመያዝ የሚደረግ ሩጫ የበዛበት ነው። ሰዎች የባለጠግነትን በረከት ለማግኘት ይጥራሉ፤ ዝናንም ለማግኘትም ብዙ መንገድ ይሄዳሉ፤ የስልጣንምም እርከን ለመውጣት ብርቱ ፍልሚያ ያደርጋሉ። በብዙ ሃይማኖቶችም ሰዎች የጽድቅን በረከት እንዲያግኙ ስረአቶችን ለመፈጸም ይታገላሉ። ሰው በራሱ በረከትን ለማግኘት የሚያደርገው መውተርተር የበረክት ጫፍ ላይ አድርሶ የሚሳርፍ አይደለም። ይልቁንም በብርቱ ጥረትና ግረት የያዙት በረከት ሲጨብጡት ምንም እየሆነባቸው ሌላ ከፍ ያለ የበረክት መሰላል ላይ ለመውጣት ያልማሉ። ፍላጎታቸውም እንደ ሚሸሽ ኢላማ ከፊታቸው አያመለጠ ይቀድማቸዋል። አንድ ጊዜ እውቁ ቱጃር ጃን ዲ ርክፌለር ለአንድ ሰው ምን ያህል ገንዘብ ይበቃዋል ተብለው ሲጠየቁ “ባለህ ላይ ጥቂት ሲጨማር” በማለት መመለሳቸው ይነገራል። ምድራዊው ሰው ሁልጊዜ ባለው ላይ ጥቂት መጨመር ይፈልጋል። የፈለገውን “ጥቂት” ሲጨምር ደግም ሌላ “ጥቂት” መጨመርን ይሻል። እንዲህ እያለ ሰው የማይሞላ የበረከት ቋት ሊምላ ሲዳክር ሕይወቱን ይፈጃል። ክርስትና ግን የሚጀምረው “ትባረካለህ” ብሎ ሳይሆን “ተባርከሃል” ብሎ ነው። ክርስትና በረከትን የመፈለግ ሩጫ ሳይሆን እንደተባረክን ተረድተን፤ የበረከታችንን ጥልቀትና ብዛት እየተረዳን በምድር እግዚአብሔር እንድፈጽመው የሰጠንን ስራ እየሰራን መኖር ነው። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር እስራኤልን “አንተ ብሩክ ነህ፣ እግዚአብሔር ያዳነው ሕዝብ እንዳንተ ያለ ማን አለ?” (ዘዳ. 33፡29 አ.መ.ት.) ይለዋል። የእስራኤል በረከት የእርሱ ጥረት ውጤት ሳይሆን በእግዚአብሔር የመመረጡ ጉዳይ ነው። የሕዝቡ በረከት እርሱ እራሱ እንጂ በእርሱ ያገኙት የምድር በረከት አልነበረም። ስለዚህም “መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፤ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው” ይለዋል። (ቁ. 27) አዲስ ኪዳንም የሚያስተምረን እግዚአብሔር “በመንፈሳዊ በረክት ሁሉ” በሰማያዊ ስፍራ እንደ ባረከን ነው። አሁን ተባርከናል! ከዚህ በኋላ የሚያስደንቀን ነገር ቢኖር የበረከቱ መገለጥ ነው። የተባረክንበት የበረከት ጥልቀት አሁን ካለን የመረዳት አቅም የሚያልፍ ነው። ነገር ግን አንድ ነገር እናውቃለን። እኛ በረከትን ለማግኘት የምንውተረተር አይደለንም። በክርስቶስ ተባርከናል። የምድር ሁኔታችን ምንም ይሆን ምን የተባረክን ሰዎች ነን። በረከታችን እሩሱ እራሱ ነው። ለዚህም ቃሉ እርሱን ማለትም መንግስቱንና ጽድቁን እንድንሻ ይመክረናል። በሰማይ በረከት የባረከን አምላክ በሚያስፈልገን የምድር በረከት አያጎድለንም። ምድራዊው ነገር ቢጎድልም እንኳ እንባቆም እንደዘመረው መንፈሳዊ በረከታችንን እያየን በመስጋና ሙላት ውስጥ እንዳንገባ አይከለክለንም። ወገኖቼ፦ የተባረከ ሕዝብ አመስጋኝ ነው። ሐዋሪያው ጳውሎስ ምንም እንኳ ይህንን መልዕክት ሲጽፍልን በእስር ላይ ቢሆንም “የባረከን ይባረክ” ብሎ ለምስጋና ይጋብዘናል። እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብሩክ ነው፤ የበረከት ቁንጮ ላይ ደርሷል፤ የበረከቱን አምላክ በምንም ሁኔታ ያከብራል። እግዚአብሔር በረከቴ ነው ስንል ስለ “አሳው” አይገደንም፤ ካስፈለገ መረባችን እስቂቀደድ ይሞላዋል። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page