top of page

ያለንን እንስጥ!

ብዙ ቅዱሳን ለምን አታገለግሉም ሲባሉ “እኔማ ለማገልገል ብቁ አይደለሁም፤ ፕሮግራም

ከተካፈልኩ መች አነሰኝ ... ወዘተ” በማለት ሲመልሱ ይደመጣል። መጽሐፍ ቅዱሳችንን

ሲንመረምር ግን የምናገኘው እውነት እግዚአብሔር የጠራቸውን ብቁ ያደርጋል እንጂ ብቁዎችን

ፈልጎ አይጠራም። ለዚህ ብዙ ማስራጃ መጥቀስ እንችላለን። ሙሴ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብጽ

እንዲያወጣ ሲጠራው አገልግሎቱን ላለመቀበል ከግዚአብሔር ጋር ብዙ ክርክር ገጥሞ ነበር። ቃሉ

“ሙሴም እግዚአብሔርን፦ ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን

ነኝ? አለው” ይለናል (ዘጸ 3፡11) በመቀጠልም ሙሴ ጥሪውን ላለመቀበል “ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ

ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ” በማለት ለእግዚአብሔር ሲመልስ እናነባለን። (ዘጸ 4፡10)

ሙሴ ያነሳ የነበረው እኔ ብቁ አይደለሁም የሚል ጥያቄ ነበር። እግዚአብሔር ግን በታምራትና

በቃል አንተ በራስህ ብቁ አይደለህም እኔ ግን ብቁ ነኝ ይለው ነበር። እግዚአብሔርም አለው

“የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ

እግዚአብሔር አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም

አስተምርሃለሁ አለው።” (ቁ. 11-12)

ወገኖቼ! እርግጥ ነው እግዚአብሔር ለመረጣቸው ብቃትን ይሰጣል እንጂ ብቁዎችን

እየመረጠ አይጠራም። አለምን የገለባበጡ ሐዋሪያት የትምሕርት ብቃትና የኃብት ብዛት ወይንም

ባለስልጣናት የነበሩ አልነበረም። ተራ ሰዎች (አብዛኞቹ ዓሳ አጥማጆች ነበሩ)። ነገር ግን መንፈስ

ቅዱስ ብቃትን ከሰጣቸው በኋላ በታላቅ ኃይልና መገለጥ የወንጌሉን እሳት አቀጣጠሉ።

እግዚአብሔር በዘመናት መካከል የጠራቸውን ሰዎች እያስታጠቀ ሃሳቡን እንዲያገለግሉ ብቃትን

ሰጥቷቸዋል። ስለዚሕም ሐዋሪያው ጳውሎስ ሲመሰክር “ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ

ቈጠረኝ፥ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ” ይላል። (1ጢሞ 1፡12)

ሐዋሪያው አገልግሎት ሹመት እንደሆነ ይነግረናል። ለዚህ ሹመት ደግም የምንበቃው

እግዚአብሔር ታማኝ አድርጎ ስለቆጠረን ነው። እኛ ታማኝ ሆነን ወይንም ብቃት ኖሮን ሳይሆን

እርሱ “ነህ”፤ “ነሽ” ስላለን ብቻ ነው። ለዚህ ሹመት የሚሆነውን ኃይልም የሚሰጠን እርሱው ነው።

እንግዲህ ሐዋሪያው እንዳለ “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነው።” (ሮሜ 11፡36)

ወገኖቼ! የኛ ድርሻ እራሳችንን ለርሱ ማቅረብ ነው። ብቃትንና ኃይልን ግን የሚሰጥ እርሱ

ነው። እርሱ በእጃችን ያሉትን ሁለት አሳና አምስት እንጀራ ከሰጠነው ታምራትን መስራት የርሱ

ፋንታ ነው። ዛሬ የት ጋር ነው እግዚአብሔር እንድንቆም የሚጠይቀን? ምንድነው በእጃችን ያለው?

ያለንን ትንሹን ነገር (እራሳችንን) ለእርሱ ብናቀርብ እርሱ ታምራትን ያደርጋል። እግዚአብሔር

በሰጠን መክሊት መጠን እንጂ ባልሰጠን መክሊት መጠን አይጠይቀንም። አንድ መክሊት ካለን

የአምስት መኪሊት ስራ አይጠብቅብንም። ነገር ግን ባለን (በተሰጠን) ልክ ለጌታ ስራ እንቁም!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page