top of page

ጸሎት አስተምረን -- አባታችን ሆይ (ክፍል አንድ)

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥

ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ

እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ...” (ሉቃ. 11፡1-2)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረው አገልግሎት ትልቅ ትኩረት ከሰጠው

ልምምድ መካከል ጸሎት ዋንኛው ነበር። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ በብዙ ስፍራ ጌታችን ሲጸልይ

ተዘግቧል። ብዙ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ተለይቶ ለብቻው እየጸለየ ከአባቱ ጋር ጊዜ ያሳልፍ ነበር።

(ማር. 4፡16፣ ሉቃ. 5፡16፣ ማቴ. 14፡23) አንዳንድ ጊዜ ደግም ለብቻው ወደ እግዚአብሔር እየጸለየ

ያድር ነበር። (ሉቃ. 6፡12) በዚህም ከላይ ባሰፈርነው ክፍል ከደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ

ጸሎትን እንዲያስተምራቸው ጌታን ሲጠይቀው እርሱ ከጸሎት ስፍራ እየተመለሰ ነበር። ጠያቂው

ሁለት ነገሮችን ያስተዋለ ይመስላል። አንደኛው በጌታ የጸሎት ሕይወት ተደንቋል። ሁለተኛው

የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ጸሎት እንደተማሩ እነርሱንም ጌታ ጸሎት እንዲያስተምራቸው ፈልጓል።

ጌታ ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስ ሰለ ጸሎት እጅግ ብዙ የምንማርበት ነው። በዚህ

ትምህርት ውስጥ በመጀመሪያ የምንመለከተው ትልቅ ቁብ ነገር ጸሎት በዋናነት የግንኙነት ጉዳይ

እንደሆነ ነው። የምንጸልየው ጠይቀን ለመቀበል ብቻ ሳይሆን፤ ጸሎት ወደ አባታችን

የምንቀርብበትና ፊቱን የምንሻበት መንገድ ነው። ልጅ ከአባቱ ጋር መሆን ደስ እንደሚለው፤ ልጅ

ከአባቱ ጋር ለመሆን ብቻ ወደ አባቱ እንደሚጠጋ ሁሉ እኛም በጸሎት ስንቀርብ የምንጠጋው ፊቱን

በመናፈቅ መሆን አለበት።

ስሊዚህ የጸሎት ትምህርት ዋናው ቁልፍ የአባትናትና የልጅን ግንኙነት ማወቅ ነው።

ለዚህ ነው ጌታችን ስትጸልዩ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ...” ብላችሁ ጀምሩ ብሎ

ያስተማረው። ስንጸልይ የምንጸልየው ወደ አባታችን ነው። የዚህ መሰረቱ ደግም በክርስቶስ ኢየሱስ

በማመን ያገኘነው የልጅነት ስልጣን ነው። (ዮሐ. 1፡12) ሐዋሪያው ጳውሎስም ሲጸልይ “በሰማይና

በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ” ይለናል። (ኤፌ. 3፡14-15)

ልጅነትን ተረድቶ በልጅነት መንፈስ ለጸሎት መቅረብ ትልቅ በረከት አለው። ምድራዊ አባት

ሁልጊዜ ለልጁ መልካም ነገር እንደሚያስብ እንዲሁ የሰማዩ አባታችን ይልቁን ለልጆቹ ሁልጌዜ

የሚበልጥ መልካም ነገርን ያስባል። ስንጸልይ የእግዚአብሔርን አባትነት በመረዳትና እርሱ

የአባትነት ሁሉ መሰረት መሆኑን በማመን መሆን አለበት። ይህም እግዚአብሔር የሕይወት ሁሉ

ምንጭና ጀማሪ መሆኑን ማወቅ ነው። አባት የህልውና ምንጭ ነው። አባት መገኛ ነው። ስለዚህ

አባታችን ሆይ ብለን ስንቀርብ አንድም በልጅነት መንፈስና ስልጣን ባለን ግንኙነት እየቀረብን

ሲሆን፤ ሁለትም እርሱ የሁሉ መገኛና ምንጭ እንደሆነም እያመንንና እያወጅን ነው። (ይቀጥላል)


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page