top of page

ጸሎት አስተምረን -- አባታችን ሆይ (ክፍል ሁለት)

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥

ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ

እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ...” (ሉቃ. 11፡1-2)

ባለፈው ሳምንት ይህንን ክፍል ስንመለከት ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን አንስተናል።

አንደኛ የምንጸልየው ጠይቀን ለመቀበል ብቻ ሳይሆን፤ ጸሎት ወደ አባታችን የምንቀርብበትና ፊቱን

የምንሻበት መንገድ ነው። በመሆኑም ጸሎት የአባትና የልጅ ግንኙነት፣ አብሮነት፣ ንግግር እንደሆነ

ተመልክተናል። ሁለተኛ ስንጸልይ የእግዚአብሔርን አባትነት በመረዳትና እርሱ የአባትነት ሁሉ

መሰረት መሆኑን በማመን እንደሆነ አይተናል። ምድራዊ አባት ሁልጊዜ ለልጁ መልካም ነገር

እንደሚያስብ እንዲሁ የሰማዩ አባታችን ይልቁን ለልጆቹ ሁልጊዜ የሚበልጥ መልካም ነገርን

ያስባል። ዛሬም በዚሁ ሃሳብ ዙሪያ ተጨማሪ ነጥቦችን እናነሳለን።

በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ብለን ስንጸልይ አንዱ የሚገለጸው ሃሳብ

የእግዚአብሔር ቅርበት ነው። እግዚአብሔር ሰማይ ዙፋኑ ነው፤ ምድርም የእግሩ መረገጫ ነች።

(ኢሳ. 66፡1) እግዚአብሔር ትልቅ አምላክ ነው። በሰማያት የምትኖር ስንል ትልቅነቱን፣

ቅድስናውን፣ ምጡቅነትና ልዕልናውን እንናገራለን። ይሁን እንጂ ይህ ትልቁ አምላክ፤ ይህ አለሙን

ሁሉ የፈጠረ አምላክ ለኛ አባታችን ነው። እግዚአብሔር አባታችን ብለን ስንጸልይ እርሱ የቅርብ

አምላክ እንደሆነ በመረዳት ነው። እርሱ ራሱ በቃሉ “እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ

አይደለሁም” (ኤር. 23፡23) እንዳለ እርሱ ከስትንፋሳችን ይልቅ ቅርብ ነው። አምላካችን ቅርብ፣

የሚሰማ፣ ፈጥኖም የሚደርስ ነው። ስለዚህም እርሱ በሰማያት የሚኖር ታላቅ አምላክ ቢሆንም ለኛ

ግን እንደ አባት ቅርብ ነው። አባታችን ነው።

ሌላው አባታችን ሆይ ብለን ስንጸልይ በውስጣችን ታላቅ መተማመን (confidence)

የሚያመጣ ጸሎት ነው። ጌታ ባስተማረው ጸሎት ላይ እንደገለጸው የምድር አባቶች እንኳ

ከሃጢያት በህርይ የተነሳ ክፉዎች ቢሆኑም እንኳ ለልጆቻቸው ጥያቄ የክፋት መልስ አይሰጡም።

የሰማዩ አባታችን ለመንጠይቀው ልጆቹ እጅግ አብልጦ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጠን ቃሉ

ያጸናልናል። መንፈስ ቅዱስ ደግም ለሁሉ ነገር መልስ የሚሆን ብቃትን ይሰጠናል። ብርታት

ለጎደለን ኋይል ይሰጠናል። እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር ወደ አባታችን ስንቀርብ በልጅ

የመተማመን እምነት ነው። በፍጹም አይተወንም፣ አይረሳንም፣ አያጎድለንም በሚል መተማመን።

እርሱ ለኛ ያለው ሃሳብ መልካም ነው፤ ከመልካምነቱ ያጠግበናል በሚል መተማመን። እርሱ

የቅርብ አምላክ ነው፤ ስንጠራው ፈጥኖ ከተፍ ይላል በሚል መተማመን። አባት ለልጁ ሁልግዜም

መልካም ነው በሚል መተማመን። የሰማዩ አባታችን ቅርብና መታመኛ ነው። (ይቀጥላል)


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page