top of page

ጸሎት አስተምረን -- ስምህ ይቀደስ (ክፍል ሶስት)

ጸሎት አስተምረን -- ስምህ ይቀደስ (ክፍል ሶስት)

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥

ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ

እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ ...” (ሉቃ. 11፡1-2)

በዚህ ክፍል ማየት እንደጀመርነው የጸሎት መሰረት የእግዚአብሔር ልጅነታችንና እርሱ

ደግሞ አባታችን የመሆኑ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ጸሎት በዋናነት የአባትና የልጅ ግንኙነት ነው።

የአባታችንን ፊት ለመሻት በልጅነት መብትና መተማመን በፊቱ እንቀርባለን። ጸሎት ወደ መንገኘቱ

ፍስሃ ያስገባናል። በዚህ ውስጥ የምንሻውን፣ የከበደንን፣ መፍትሔ የምንፈልግበትን ጉዳይም በፊቱ

እናፈሳለን። እርሱም አባት ለልጁ መልካም ስጦታን እንደሚሰጥ ሁሉ ጸሎታችንን ይሰማናል፣

ይመልስልናል። ዛሬ በዚህ ጸሎት ውስጥ ያለውን ሌላ ሃሳብ እናነሳለን። ስንጸልይ ሌላው

የምናደርገው ነገር የአባታችን ስም መቀደስ ነው።

ወላጆቻችን ባወጡልን ስም ውስጥ መልካም ምኞት አለ። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ስም

ከግብር ላይገጥም ይችላል። ትግስት ክብሪት ልትሆን ትችላለች፤ ተፈሪ ፈሪ ሊሆን ይችላል።

እግዚአብሔር ግን እንደ ስሙ እንደዚያው ነው። ኤልሻዳይ የተባለው ሁሉን የሚችል አምላክ

ስለሆነ ነው፤ አዶናይ የምንለው ጌታ ስለሆነ ነው፤ ጂዮቫ ጃራ የምንለው ሰጪ አምላክ ስለሆነ ነው፤

ጂዮቫ ሻሎም የምንለው እርሱ የሰላም አምላክ ሰለሆነ ነው፤ ጂዮቫ ራፋ የምንለው እርሱ ፈዋሽ

አምላክ ስለሆነ ነው፣ ጂዮቫ ራህ የምንለው እርሱ እረኛ አምላክ ስለሆነ ነው፤ ጂዮቫ ጻድቂኑ

የምንለው እርሱ ጽድቃችን ስለሆነ ነው። በእግዚአብሔር ስም ውስጥ ማንነቱ አለ። እርሱ ስሜ

“ያለና የሚኖር” (ዘጸ. 3፡14) ነው ሲል እርሱ ዘላለማዊ አምላክ ስለሆነ ነው።

እኛ በጸሎታችን በእግዚአብሔር ስምና ማንነት ላይ የምጨምረውም ሆነ የምንቀንሰው

ነገር የለም። ነገር ግን “አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ” ስንል ለአባታችን ለግዚአብሔር ስም እኛ

የምንሰጠውን የተለየ (የተቀደሰ) ስፍራ መግለጻችን ነው። ጸሎቱ የእግዚአብሔር ስም በኛ ሕይወት

እንዲቀደስ፣ እግዚአብሔርን እንደ ስሙ እንድናከብረውና እንድናመልከው፣ የስሙ ልዕልናና ክብር

በሕይወታችንና በኑሮአችን እንዲገለጽ መፍቀዳችን ነው። የምንቀድሰው ነገር የተለየ አድርገን

(ለይተን) የምናከብረው ነው። በብሉይ ኪዳን ሰዎችም እቃም ለእግዚአብሔር ይቀደሱ (ለርሱ

ክብር ብቻ ይሆኑ) ነበር። በዚህ ጌታ ባስተማረንም ጸሎት ውስጥ “ስምህ ይቀደስ” ስንል

የእግዚአብሔርን ስም በሕይወታችን ያለውን በምንም በማንም የማይተካ፣ የከበረና ዋንኛ ስፍራ

እንደያዘ ማወጃችን ነው። በስሙ ውስጥ ያለውን ማንነቱን፣ አምላክነቱን፣ አዳኝነቱን፣ ፈዋሽነቱን፣

ግርማውን፣ ሁሉን ቻይነቱን ... ተቀብለን በህይወታችን የተለየውን የከበረ ስፍራ መስጠታችን

ነው። ስሙ በሕይወታችን የተቀደሰ ይሁን! አሜን! (ይቀጥላል)


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page