top of page

ጸሎት አስተምረን -- መንግስትህ ትምጣ (ክፍል አምስት)

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥

ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ

እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... መንግስትህ ትምጣ ...” (ሉቃ. 11፡1-2)

ባለፈው ሳምንት እንዳየነው ጌታ ባስተማረን ጸሎት ውስጥ የምንጸልየው አንዱ ጸሎት

“መንግስትህ ትምጣ” ብለን ነው። ዛሬ ስለዚህ ጸሎት ተጨማሪ ሃሳቦችን እናያለን።

መንግስትህ ትምጣ ብለን ስንጸልይ የእግዚአብሔር ኃይልና ሕልውና በሕይወታችን፣

በቤተ ክርስቲያን እና በምንኖርበት አካባቢ እንዲገዛ መፍቀዳችን ነው። የመንግስታት ግንኙነት

የኃይል ግንኙነት ነው። አንድ መንግስት ተጽንኦ በሚያሳድርበት ስፍራና ሁኔታ ሌላ መንግስት

ተጽንኦ ማሳረፍ አይችልም። የእግዚአብሔር መንግስት በኃይል በምትሰራበት ስፍራ የጨለማው

መንግስት መስራት አይችልም። የግዚአብሔር መንግስት የብርሃንና የጽድቅ መንግስት ስልሆነ

የጨለማ ኃይል በፊቱ ሊቆም አይችልም። ስለዚህ የጌታ መንፈስ ባለበት ስፍራ ሁሉ አርነት አለ።

ስለዚህ ነው የእግዚአብሔር መንግስት በምትገዛበት ስፍራ ሁሉ ሰዎች ከተለያየ እስራት የሚፈቱት።

መንፈስ ቅዱስ በሚሰራበት ስፍራ የሚገለጠው የእግዚአብሔር መንግስት ነው። ጌታችን “እኔ ግን

በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ

እናንተ ደርሳለች” ብሎናል። (ማቴ. 12፡28) አጋንንት ሰዎችን ለቀው የሚወጡት ከእነርሱ

በሚበልጥ ኃይል ብቻ ነው። ያም ደግም የእግዚአብሔር መንግስት ኃይል ነው። ቤተ ክርስቲያን

በምድር የእግዚአብሔር መንግስት መገለጫ ስለሆነች የገሃነብ ደጆች አይችሏትም። ያቆማትና

የሚደግፋት ብርቱ የሆነው የእግዚአብሔር መንግስት ኃይል ነው።

ሌላው ስለ እግዚአብሔር መንግስት ጉዳይ መረዳት ያለብን ነገር የእግዚአብሔር

መንግስት ከምንም በላይ የምንፈልጋት መሆን እንዳለበት ነው። ለዚህ ነው ቃሉ “መንግስትህ

ትምጣ” ብላችሁ ጸልዩ የሚለን። ስለዚህም አስቀድመን የእግዚአብሔርን መንግስትና ጽድቅ

መፈለግ አለብን። ጌታ በብዙ ምሳሌ እንዳስተማረው የእግዚአብሔር መንግስት ያለንን ሁሉ ሸጠን

እንደምንገዛት የከበረ መዝገብ ነች። የእግዚአብሔር መንግስት ያለንን ሁሉ ሸጠን እንደምንገዛት

የከበረ እንቁ ነች። የሚተካከላት የለም። በክርስቶስ ያገኘነውን በመንግስቱ ውስጥ የመግባት

ሕይወት በምንም ልንለውጠው ወይንም ከምንም ጋር ልናነጻጽረው አንችልም። ሐዋሪያው

ጳውሎስ በምድር ሊመካበት ከሚችለው ነገር ሁሉ በላይ በክርስቶስ ያገኘው ሕይወት እንደሚልጥ

መስክሯል። እንዲያው ስለ ክርስቶስ ሌላውን ሁሉ እንደ ጉድፍ (ፋንድያ) እንደሚቆጥረው

ተናግሯል። ለኛም እንዲሁ ነው። የተቀበልነው ሕይወት፣ በወንጌል አምነን የግዚአብሔር ልጆችና

የመንግስቱ ዜጎች መሆናችን የከበረ ነው። እግዚአብሔር ሆይ “መንግስትህ ትምጣ።” (ይቀጥላል)


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page