top of page

ጸሎት አስተምረን -- መንግስትህ ትምጣ (ክፍል ስድስት)

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... መንግስትህ ትምጣ ...” (ሉቃ. 11፡1-2)

“መንግስትህ ትምጣ” ብለን ስንጸልይ የእግዚአብሔር ኃይልና ሕልውና በሕይወታችን፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምንኖርበት አካባቢ እንዲገዛ መፍቀዳችን እንደሆነ አይተናል። የእግዚአብሔር መንግስት ከምንም በላይ የምንፈልጋት መሆን እንዳለበትም አይተናል። ዛሬ ደግም የእግዚአብሔርን መንግስት መፈለግ ምን ማለት እንደሆነ እናያለን።

ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 14 ቁጥር 17 ላይ እንደገለጻት “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችም።” በዚህ ክፍል የእግዚአብሔር መንግስት ምን እንደምትመስል ቃሉ ያስተምረናል። በመጀምሪያ አሉታዊውን ሃሳብ ብንመለከት የእግዚአብሔር መንግስት የመብልና የመጠጥ ጉዳይ አይደለችም። በክፍሉ አውድ ስንመለከተው የምንበላው ወይንም የምጠጣው ነገር እርስ-በርስ ካለን ግንኙነት አንጻር ፋይዳ ሊኖረው ይችል እንደሆነ እንጂ በራሱ በእግዚአብሔር መንግስት የምንመላለስበትን አቋም አያመለክትም። ሌሎችን የሚያሰናክል ነገር ማድረግ መልካም አይደለም ነገር ግን ወደ አፍ የሚገባው ጌታችን አንዳስተማረው የሚያረክስም፣ የሚቀድስም አይደለም። እርሱ በሆድ አልፎ በእዳሪ ይወጣል። ይልቁንም ከአፍ የሚወጣው ከልብ ይወጣልና ሰውን የሚያረክሰው ያ ነው። (ማቴ. 15፡ 11፣ 17፣ 18) በሌላ መልኩ ደግም የእግዚአብሔር መንግስት ጉዳይ ምድራዊ የሆነ የኑሮ መብልና መጠጥ ጉዳይ አይደለም። እርግጥ ነው መንግስቱንና ጽድቁን ስንፈልግ እግዚአብሔር ለኑሮ የሚያስፈልገንን ሁሉ አያሳጣንም። እንዲያውም ይጨምርልናል። (ማቴ. 6፡ 33) ንጉስ ዳዊትም “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” ብሏል። በጎልምስና እና በእርጅና መካከል በትንሹ አርባ አመት አለ። ዳዊት የሕይወት ዘመን ተመክሮውን ሲካፍለን የሚለው ነገር እግዚአብሔርን የሚፈልግ ሰው ተጥሎ እንዳላየ ነው። የሚቀድመውን ካስቀደምን እግዚአብሔር መኖሪያችን ይሆንልናል።

በአውንታዊ መልኩ ደግም የእግዚብሔር መንግስት በሶስት ሃሳቦች ተገልጻለች። የእግዚአብሄር መንግስት አንደኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ ናት። ሁለተኛ የእግዚአብሔር መንግስት የእግዚአብሔር ሰላም ናት። ሶስተኛ የእግዚአብሔር መንግስት በመንፈስ ቅዱስ የሚሆን ደስታ ናት። እንግዲህ የእግዚአብሔርን መንግስት ስንፈልግና መንግስትህ ትምጣ ስንል እየፈልግን ያለነው የግዚአብሔርን ጽድቅ፣ ሰላምና በመንፈስ ቅዱስ የሚሆንን ደስታ ነው። እነኚህን ሃሳቦች በዝርዝር በሚቀጥሉት ጽሑፎች እናያለን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page